ቀጥታ፡

በአካባቢያችን ለሚከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ውጤታማነት ክትትልና ድጋፋችንን እናጠናክራለን-የምክር ቤት አባላት

ጂንካ፤ጥቅምት 7/2018 (ኢዜአ) :- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብን የልማት ጥያቄ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ለመመለስ እየተከናወኑ ያሉ ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የክትትልና ድጋፍ  ስራቸውን እንደሚያጠናክሩ በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤት አባላት ተናገሩ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤቶች የጋራ ምክክር ፎረም በጂንካ ከተማ ተካሄዷል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤት አባላት በአካባቢያቸው እየተከናወኑ ለሚገኙ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ውጤታማነት የሚያደርጉትን ድጋፍና ክትትል አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

የዲላ ሪጂዮ ፖሊሲ ከተማ አስተዳደር ምክትል አፈ-ጉባኤ አለማየሁ ጂግሶ፤ መንግስት የከተማውን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉ ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።


 

በከተማው የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ለስራ ዕድል ፈጠራ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረው የልማት ስራዎቹ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የድጋፍና ክትትል ተግባራቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።

በአርብቶ አደሩ አካባቢ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚያሸጋግሩ ሰፋፊ የግብርና ልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ የገለፁት ደግሞ የደቡብ ኦሞ ዞን ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ዶቦ አዊኖ ናቸው።


 

የደቡብ ኦሞ ዞን ዝናብ አጠር ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ መሆኑን የገለፁት ምክትል አፈ-ጉባኤዋ፤ አርብቶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ በመስኖ ልማት እንዲሰማራ መንግስት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚተገበሩ የግብርና ልማት ስራዎች የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመሆን የአርብቶ አደሩን ኑሮ እየለወጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በአሪ ዞን የገሊላ ከተማ አስተዳደር አማካሪ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ታጋይ ፍላቴ፥ በአካባቢው እምቅ የግብርና አቅም እንዳለ ጠቅሰው በአካባቢው ዓመቱን ሙሉ ማልማት የሚያስችል ምቹ የአየር ጠባይ እና በቂ የውሃ ሀብት አለ ብለዋል።


 

እነዚህን አቀናጅቶ በማልማት የአርሶ አደሩን ኑሮ ለመለወጥ እየተሰራ ያለው አበረታች ስራ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን የተጠናከረ የድጋፍና ክትትል ስራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በአካባቢው ስንዴና ገብስን የመሳሰሉ ሰብሎች በኩታ ገጠም በስፋት እየለሙ መሆኑን ጠቅሰው፥ ምርቱን ለኢንዱስትሪዎች በማቅረብ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በአካባቢው ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የሚያስችሉ ሰፋፊ የግብርና ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የኮንሶ ዞን ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ገልገሎ ኦቶማ ናቸው።


 

በዞኑ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ጠቅሰው፥ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረው ስራ ውጤት ማምጣት መጀመሩን ጠቅሰዋል።

በዞኑ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው የህዝቡን አዳጊ ፍላጎት ለማሟላት መንግስት እያደረገ ያለው ጥረት ከግብ እንዲደርስ ምክር ቤቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም