ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ያገኘናቸው የተሻሻሉ የቡናና የእንስሳት ዝርያዎች ተጠቃሚ አድርገውናል-አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ያገኘናቸው የተሻሻሉ የቡናና የእንስሳት ዝርያዎች ተጠቃሚ አድርገውናል-አርሶ አደሮች

ዲላ ፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ)፦ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በድጋፍ ያገኟቸው የተሻሻሉ የቡናና የእንስሳት ዝርያዎች ተጠቃሚ እንዳደረጓቸው የጌዴኦ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ አገልግሎት ባከናወናቸው የግብርና ሥራዎች የመስክ ምልከታና ውይይት ተካሂዷል።
በዚህም የአካባቢውን አርሶ አደር ተጠቃሚነት ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲው ያቀረባቸው የተሻሻሉ የቡናና የእንስሳት ዝርያዎች ውጤታማ መሆናቸው ተመልክቷል።
በመስክ ምልከታው ወቅት አርሶ አደሮቹ እንደገለጹት ከዩኒቨርሲቲው በድጋፍ ያገኟቸው የተሻሻሉ የቡናና የእንስሳት ዝርያዎች በተሻለ ተጠቃሚ እያደረጓቸው ነው።
የይርጋጨፌ ወረዳ አርሶ አደር ፍሬ ቀቀቦ ለኢዜአ እንደገለጹት ከዩኒቨርሲቲው ባገኙት የተሻሻለች ጊደር የላም እርባታ ሥራቸውን መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ጊደሯ ወልዳ ተጨማሪ ጥጃ ማግኘታቸውንና በቀን ከ10 ሌትር በላይ ወተት እያገኙ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት ኑሯቸው በግብርና ልማት በተለይ በቡናና በእንሰት ብቻ ተወስኖ እንደነበር አስታውሰው፣ በተጨማሪነት ከጀመሩት የእንስሳት እርባታ ሥራ የሚያገኙትን ወተት ለቤት ውስጥ ፍጆታና ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት ከ15 ሺህ በላይ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ከዩኒቨርሲቲው የምርምር ጣቢያ ማግኘታቸውን የገለጹት ሌላው አርሶ አደር ዳንኤል ሾንጦጦ ናቸው።
ከተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች በሄክታር አስከ 15 ኩንታል የቡና ምርት በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ከዩኒቨርሲቲው ባገኙት ስልጠና የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን በማፍላት ለአካባቢው አርሶ አደሮች በሽያጭና በነጻ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ፍላጎት መሠረት ያደረገ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ ዞኑ ለሚታወቅበት የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና የግብርና ልማት ትኩረት በመስጠት ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑን አንስተዋል።
በዞኑ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚሰሩ ሥራዎችን ከማገዝ ባለፈ በተፋሰስ ልማትና በግብርና ምርታማነት ላይ በቅንጅት የሚሰራውን ሥራ በቀጣይ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው የትኩረት መስኩን ከማህበረሰብ ጋር በማቀናጀት የህብረተሰቡን ችግሮች የሚፈቱ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኤልያስ ዓለሙ (ዶ/ር) ናቸው።
ባለፈው ዓመት ብቻ ከ 711 ለሚበልጡ አርሶ አደሮች ከ400 ሺህ በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን የማሰራጨትና ዘመናዊ አሰራር የማላመድ ሥራዎች መከናወኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።
እንዲሁም የሌማት ትሩፋት ትግበራን ለማስፋት ሞዴል መንደር በመመስረት የተሻሻሉ የወተት ላሞችን ልማት ከማከናወን ባለፈ 10 ጊደሮን ለአርሶ አደር መሰራጨቱን ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው በአራት የትኩረት መስኮች ከ148 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በቀጥታ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።