የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋም አዲሱን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ፕሮጀክት ለመደገፍ ጠንካራ ፍላጎት አሳይቷል- የገንዘብ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋም አዲሱን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ፕሮጀክት ለመደገፍ ጠንካራ ፍላጎት አሳይቷል- የገንዘብ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2018 (ኢዜአ)፦ የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ የሚገነባውን አዲስ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ፕሮጀክት ለመደገፍ ጠንካራ ፍላጎት ማሳየቱን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ኢትዮጵያ እና የፋይናንስ ኮርፖሬሽኑ የአየር ማረፊያ በፋይናንስ ለመደገፍ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተከታታይ ውይይቶችን ለማድረግ መስማማታቸውንም ገልጿል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ይገኛል።
በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በዓመታዊ ስብስባው ላይ እየተሳተፈ ነው።
ኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (DFC) ከስብስባው ጎን ለጎን በኢትዮጵያ የሚገነባውን እየሰፋ ያለውን የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዘርፍ እና አጠቃላይ የኢኮኖሚ ልማት ግቦችን መደገፍ ያለመውን አዲሱን ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያ ፕሮጀክት ግንባታ የፋይናንስ ትብብርን ማጠናከር ያለመ በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ ምክክር አድርገዋል።
በውይይቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ የተመራው የክፈተኛ የመንግስት ልዑክ እና የአሜሪካው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ልማት ኮርፖሬሽን ከፍተኛ አመራሮች አዲሱን አየር ማረፊያ በፋይናንስ መደገፍ በሚቻልባቸው እድሎች ላይ መክረዋል።
በኢትዮጵያ በግንባታ ላይ ያሉ እና በቀጣይ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመት እና የፋይናንስ አቅርቦት ላይም ተወያይተዋል።
የአየር ማረፊያ ፕሮጀክቱ የተጓዦች እና የካርጎ አገልግሎት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳድግ፣ በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ያለውን መጨናነቅ የሚቀንስ እና በአፍሪካ ቀንድ ቁልፍ የሎጅስቲክስ ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል ነው።
በውይይቱ ወቅት የፋይናንስ ኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቱን በፋይናንስ፣ የኢንቨስትመንት ዋስትና በመስጠት እና ከአሜሪካ የግሉ ዘርፍ ጋር በመሆን የመደገፍ ጠንካራ ፍላጎት አሳይቷል።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ የአሜሪካው የፋይናንስ ተቋም በኢትዮጵያ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት በተለይም በአቪዬሽን ዘርፍ ለመሰማራት ያሳየውን ፍላጎት መልካም የሚባል መሆኑን አንስተው፤ ይህም ለብሄራዊ ልማት እና ቀጣናዊ ተወዳዳሪነት ቁልፍ መሆኑን አመልክተዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያ እና የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽኑ ጠንካራ አጋርነት በመፍጠር ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ኢኮኖሚ ዘላቂ ጥቅሞችን ለማስገኘት ወሳኝ የሚባል እርምጃ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።
ሁለቱ ወገኖች ለአዲሱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተጨባጭ የፋይናንስ መዋቅር ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ቀጣይ ውይይቶችን ለማድረግ ተስማምተዋል።
ውይይቱ አሜሪካ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜን በፋይናንስ የመደገፍ የሚያስችል አጋርነት የመፍጠር የጋራ ራዕይ የሚያመላክት እንደሆነ ተገልጿል።
የሁለትዮሽ ውይይቱ የአሜሪካው የፋይናንስ ተቋም ከአፍሪካ ጋር ያለውን ትብብር የማሳደግ አካል እንደሆነም ተመላክቷል።