ሜሪጆይ ኢትዮጵያ በሀዋሳ ያስገነባው የኩላሊት እጥበት ማእከል ተመርቆ ስራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ሜሪጆይ ኢትዮጵያ በሀዋሳ ያስገነባው የኩላሊት እጥበት ማእከል ተመርቆ ስራ ጀመረ

ሀዋሳ፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ)፦ ሜሪጆይ ኢትዮጵያ በሀዋሳ ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባው የኩላሊት እጥበት ማእከል ተመርቆ ስራ ጀመረ።
የሲዳማ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እና የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የኩላሊት እጥበት ማእከሉን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት ወደ ስራ የገባው የኩላሊት እጥበት ማእከሉ በቀን እስከ 90 ሰው ማስተናገድ ይችላል ተብሏል።
የማእከሉ አገልግሎት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገና በአነስተኛ ክፍያ ህክምና እንደሚሰጥም ተገልጿል።
የኩላሊት እጥበት ማእከሉን ሜሪጆይ ኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን እንዲሁም መላውን ማህበረሰብ በማስተባበር ያስገነባው መሆኑም ተመልክቷል።
በሂደቱም የሲዳማ ክልልና የፌደራል መንግስት ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተጠቅሷል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይም የፌደራል፣ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላትና የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።