በከተማ አስተዳደሩ የተከናወኑ የሰላምና የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በከተማ አስተዳደሩ የተከናወኑ የሰላምና የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው

ደብረ ብርሃን ፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ)፦ በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የተከናወኑ የሰላምና የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆናቸውን የአስተዳደሩ ምክር ቤት አመለከተ።
የደብረ ብርሃን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 13 ዓመት 47ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ መንግስቱ ቤተ እንዳሉት፤ በከተማ አስተዳደሩ የተከናወኑ የሰላምና የልማት ስራዎች የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው።
በኢንዱስትሪና በኢንቨስትመንት ዘርፉ ተኪ ምርቶችን በማምረት ገበያን የማረጋጋት ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው ብለዋል።
የንግድና ገበያ ማዕከላት ግንባታ ስራዎች ዘመናዊ የግብይት ስርዓት ለመዘርጋት አይነተኛ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።
እነዚህና ሌሎች ተግባራት በበጀት ዓመቱ ሰላምን ከማፅናት ባሻገር የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተለይም በመንግስት ተቋማት የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ መጓደል ችግሮችን በተደራጀ አግባብ በመፍታት ለህዝቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ይገባል ብለዋል።
የከተማዋን እድገት ለማፋጠን ግብርን አሟጦ በመሰብሰብ የልማት ዕቅድ በጥራትና በተደራሽነት መተግበር እንደሚገባም አመልክተዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት እንዳሉት፤ ባለፉት ወራት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተከናወኑ የልማትና ሰላምን የማረጋገጥ ተግባራት ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
አሁን ላይም የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ፣ የተቋማትን የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም የማሳደግ ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም 269 ለሚሆኑ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከመስጠት ባሻገር 18 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በከተማው የተከናወነውን የኮሪደር ልማት ወደ ገጠሩ በማስፋት ለ1 ሺህ የቤተሰብ መሪዎች ዘመናዊ ቤቶች እንዲገነቡ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
እንዲሁም ሁለት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት 5 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታና መሰል የልማት ተግባራት በትኩረት ይከናወናሉ ሲሉም አብራርተዋል።
ምክር ቤቱ ጉባኤውን በነገው ዕለት እንደሚያጠናቅቅ ታውቋል።