ቀጥታ፡

የወባ በሽታን ለመከላከል እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል

ደሴ ፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ) ፡-በደቡብ ወሎ ዞን የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ ሁሉም አካባቢውን ከማፅዳት ጀምሮ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተገለጸ።

በዞኑ በሀርቡ ከተማ አስተዳደር የማሕበረሰብ አቀፍ የወባ መከላከልና ቁጥጥር የዘመቻ ሥራ ዛሬ ተጀምሯል።


 

በማስጀመሪያው መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አሊ ይማም እንዳመለከቱት፤ በዞኑ ለወባ በሽታ ተጋላጭ ወረዳዎች ተለይተው የመከላከል ሥራው በትኩረት እየተከናወነ ነው።


 

በዚህም የወባ በሽታን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ሕብረተሰቡ አካባቢውን በማጽዳት፣ ያቆረ ውሃን በማፋሰስ፣ በማዳፈንና ደረቅ ቆሻሻን በማቃጠል የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል።

ለዚህም ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ተግባሩን በመገምገም ተገቢው ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው በለጠ፤ በዞኑ ከመስከረም አጋማሽ እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ የወባ በሽታ የሚስተዋልበት ወቅት በመሆኑ ጥብቅ የአካባቢ ቅኝት ስራ ማካሄድ አስፈላጊ ነው ብለዋል።


 

ለወባ ተጋላጭ 7 ወረዳዎች ተለይተው ሕብረተሰቡን በማስተባበር የተካሄደው የመከላከል ስራ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል። 

የተገኘውን የመከላከል ስኬት እስከ መጨረሻው ለማዝለቅም ሕብረተሰቡ ሳይዘናጋ በአካባቢው ውሃ የሚያቁር ሥፍራን ማፋሰስ፣ ማዳፈንና ቆሻሻን ማቃጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ቀደም ሲል የተሰራጨውን አጎበር በአግባቡ መጠቀምና ሕመም ሲሰማም ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ህክምና ማግኘት  እንዳለበትም አመልክተዋል።

በጤና ባለሙያዎች ምክር ታግዘን አካባቢያችንን እያጸዳን፣ ውሃ የሚያቁሩ አካባቢዎችንም እያፋሰስን የወባ በሽታን እየተከላከልን ነው ያሉት ደግሞ የሀርቡ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሽዋዬ ያሲን ናቸው።


 

ባለፈው ዓመት ልጃቸው በወባ በመታማሙ ለችግር እንደታዳረጉ አስታውሰው፤  ዘንድሮ የአካባቢውን ሕብረተሰብ በማስተባበር የአካባቢያችንን ጽዳት በመጠበቅ በሽታውን እንድንከላከል ረድቶናል ብለዋል።

ሌላዋ የዚሁ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ራቢዓ ይመር በበኩላቸው ፤ አካባቢያችን ለወባ ተጋላጭ በመሆኑ የወባ ትንኝ መራቢያዎችን እያጸዳን፣ ጤናችንን እየጠበቅን እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል።


 

ዛሬ የተጀመረውን ዘመቻም በማስቀጠል በሳምንት ሶስት ቀን አካባቢያቸውን በማጽዳት ራሳቸውንና አካባቢያቸውን ከወባ በሽታ ለመከላከል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ ኣካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም