ህግ የማስከበር እርምጃው በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል- አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ህግ የማስከበር እርምጃው በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል- አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር)

ገንዳውሃ፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል መንግስት የጀመረው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕርግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
በምዕራብ ጎንደር ዞን ከገንዳውሃ፣ መተማ ዮሐንስ ከተማና መተማ ወረዳ ከተውጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሰላም፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕርግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር)፤ በክልሉ ሰላም ለማምጣት መንግስት ለሰላማዊ አማራጭ ጭምር እድሎችን በማመቻቸት ብዙ መስራቱን አንስተዋል።
የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበልም በጫካ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በመፍታት ሰላማዊ ሕይወት እየኖሩ መሆኑን ገልጸው ፤ በዘረፋና እገታ ተግባራቸው የቀጠሉ ጽንፈኞች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግስት ሕግ የማስከበር እርምጃውን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
የመከላከያ ሰራዊት 504ኛ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴየር ጄኔራል ሙላው በየነ፤ የመንግስትን የሰላም እድሎች በማይጠቀሙ ፅንፈኞች ላይ ሰራዊቱ ጠንካራ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ዘረፋና ግድያ በመፈፀም የሕዝብን ሰላም እያናጋ ያለው ጽንፈኛ ቡድን ላይ የሚወሰደው ሕግ የማስከበር ተግባር ይቀጥላል ብለዋል።
የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ በሪሁን መንግሥቱ፤ የሕዝቡን ሰላምና ደሕንነት በማስጠበቅ ረገድ ማሕበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ የሕግ ማስከበር ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በዚሕ ረገድ የክልሉ ሕዝብ ከጸጥታ አካላት ጎን በመሰለፍ ያሳየውን ቀና ትብብር አድንቀው በቀጣይም ድጋፉ እንዳይለይ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አንዳርጌ ጌጡ፤ የዞኑን ሰላም ለመጠበቅ ከፌዴራልና ከክልል ፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚሕም በአካባቢው አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን አንስተው፤ የሕዝቡ የሰላም ጥረት መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የግጭትና ጦርነት አዙሪት አብቅቶ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ብለዋል።
ከጦርነት ውድመት እንጂ የሚገኝ ትርፍ አለመኖሩን ሁላችንም እንገነዘባለን ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ፤ ለዘላቂ ሰላም መስፈን የጸጥታ ሃይሉን እናግዛለን ሲሉም አረጋግጠዋል።