ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር እና የጋራ ትርክትን ለመገንባት በሚከናወኑ ተግባራት ሙያዊ ኃላፊነታችንን በብቃት እንወጣለን

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር እና የጋራ ትርክትን ለመገንባት በሚከናወኑ ተግባራት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት እንደሚወጡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራሮችና ሰራተኞች ቃል በመግባት አረጋገጡ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራሮችና ሰራተኞች "ብሔራዊ ጥቅምና የጂኦስትራቴጂ ቁመና" በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ውይይት አካሄደዋል።


 

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ እንዳሉት፤ ጋዜጠኞች ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር በሚያስችሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የበለጠ መስራት አለባቸው።

የወል ትርክትን ለመገንባትና የሀገር ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን በመስራት ሙያዊ ሃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።


 

ታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቁ የቀደመውን ትርክት መቀየር ያስቻለ መሆኑን አንስተው፤ የኢትዮጵያን የነገ መስመር የሚቀይሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ ህዝብና ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላት ሃገር ብትሆንም የባህር በር እንደሌላት አንስተው፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ሙያዊ ሀላፊነታቸውን በብቃት መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ ያላትን ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ለማረጋገጥ የኢዜአ ሰራተኞች ከዜግነት በተጨማሪ ሙያዊ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ነጋሲ አምባዬ የውይይት ጽሁፍ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ በድህረ እውነት ዘመን የአገር ብልፅግናን ለማረጋገጥ ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ ሙያዊ ሃላፊነትን በሚገባ መወጣት ያስፈልጋል።


 

ብሔራዊ ጥቅም የሀገር ህልውና ደህንነት እና ብልፅግና ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው፤ የብሔራዊ ጥቅምና ጂኦስትራቴጂያዊ ቁመና የህዝብና የትውልድ አጀንዳ ለማድረግ የበኩላችንን ሚና ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የማንሰራራት ምዕራፍ ላይ ያለች እና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እያከናወነች መሆኗን ያነሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተፈራ በቀለ ናቸው።

ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቁ ስራዎችን መስራት ከመገናኛ ብዙሃን  የሚጠበቅ መሆኑንም ነው የገለፁት።


 

የኢዜአ ሰራተኞች በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተገነቡ ያሉ የልማት ስራዎች እንዲሳኩና የጋራ ትርክትን ለመገንባት የበኩላቸውን ሚና አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር እና የጋራ ትርክትን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም