በኢትዮጵያ 100 ከተሞችን ተደራሽ የሚያደርግ የዲጂታል አድራሻ ስርዓት ተግባራዊ ሊደረግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ 100 ከተሞችን ተደራሽ የሚያደርግ የዲጂታል አድራሻ ስርዓት ተግባራዊ ሊደረግ ነው

ጎንደር ፤ ጥቅምት 7/2018 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ 100 ከተሞችን ተደራሽ የሚያደርግ የዲጂታል አድራሻ ስርዓት ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ኢንስቲትዩቱ ጎንደር ከተማን የዲጂታል አድራሻ ስርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ዛሬ ተፈራርሟል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላቸው ፀሐይ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን ታላላቅ ከተሞች ዘመኑን የዋጀ የዲጂታል አድራሻ ስርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡
ኢንስቲትዩቱ በ10 ዓመት ውስጥ 100 ከተሞችን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ ነድፎ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባን ጨምሮ በርካታ የክልል ከተሞችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡
በአማራ ክልል የደብረ ብርሃንና የኮምቦልቻ ከተሞች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተው፤ በደሴና ወልዲያም ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
የከተሞች የዲጂታል አድራሻ ስርዓት ከተሞች ወደ ስማርት ሲቲ የሚያደርጉትን የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያፋጥን ከመሆኑም በላይ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም መዳረሻ ለሆኑ ከተሞች የላቀ አበርክቶ አለው፡፡
ዲጂታል የአድራሻ ስርዓት መኖሪያ ቤቶችን፣ መንገዶችንና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያሉበትን መገኛ ቦታ ርቀትና አቅጣጫ በቀላሉ ለማመልከት የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
ዲጂታል የአድራሻ ስርዓት ለከተሞች ፈጣን እድገትና ለውጥ ቁልፍ የቴክኖሎጂ መሳሪያ ነው ያሉት የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ናቸው፡፡
የጎንደር ከተማ ሰባት ታላላቅና ታዋቂ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች እንዳሏት ጠቅሰው፤ እነዚህን የቱሪዝም የመስህብ ሀብቶች በማስተዋወቅ ቱሪስቶች ስፍራዎቹን በቀላሉ እንዲጎበኙ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ቴክኖሎጂ ነው ብለዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ለፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት ከኢንስቲትዩቱ ጋር በቅርበት የሚሰራ ሲሆን በመጪው ጥር ወር በከተማው በድምቀት ለሚከበረው የጥምቀት በዓል ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመግባቢያ ስምምነት ሰነዱ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የኢንስቲትዩቱ የስራ ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች ተገኝተዋል፡፡