ቀጥታ፡

የአፍሪካ የክህሎት ልማት ስትራቴጂ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ የክህሎት ልማት ስትራቴጂ በአህጉሪቱ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራት ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ ወሳኝ ድርሻ እንደሚያበረክት ተገለጸ፡፡

የአፍሪካ የክህሎት ልማት ስትራቴጂ በሁለተኛው የአፍሪካ የክህሎት ሳምንት መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ መበሰሩ ይታወቃል፡፡

ስትራቴጂው በመላው አፍሪካ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናን ጥራት ለመጠበቅና ተደራሽነቱን ለማስፋት ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ስለ ክህሎት ልማት ስትራቴጂው አስፈላጊነት ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡


 

በስራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ ዋና አማካሪ ተሾመ ለማ(ዶ/ር)፤ የአፍሪካ የክህሎት ልማት ስትራቴጂ ከአፍሪካ የ2063 አጀንዳ ጋር ትስስር ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ግቦች ጋር የተጣጣመ፣ አካታች እና ፈጠራን መሰረት ያደረገ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

ስትራቴጂው ከፈረንጆች 2025 እስከ 2034 ድረስ በአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ተፈጻሚ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

አፍሪካውያን ወጣቶችን ጊዜውን የዋጀ ክህሎት በማላበስ በዓለም አቀፍ የስራ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የዜጎችን ክህሎት ለማልማት ደግሞ አፍሪካውያን የቴክኒክና ሙያ ተቋሞቻቸውን ማስፋትና ጥራታቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው አመላክተዋል፡፡

ስትራቴጂው በአህጉሪቱ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራት ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡


 

የኡጋንዳ የቴክኒክ ትምህርትና ስልጠና ኮሚሽነር ሎይ አባኔይ በበኩላቸው፤ ስትራቴጂው የአፍሪካ ሀገራት የተጣጣመ የትምህርትና ስልጠና ስርዓት እንዲኖራቸው ያስችላል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ሀገራት የራሳቸውንና ቀጣናዊ ስትራቴጂ ለማዘጋጀት እንደ መነሻ ማዕቀፍ ሆኖ እንደሚያገለግልም ገልጸዋል፡፡

ስትራቴጂው ማንኛውም ብቃት ያለው ዜጋ ድንበር ሳይገድበው በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ተንቀሳቅሶ ለመስራት እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም