ቀጥታ፡

በተያዘው በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ስማርት ቴክኖሎጂዎችን ለደንበኞች ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል - ኢትዮ ቴሌኮም

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ)፦ በተያዘው በጀት ዓመት ከ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ስማርት የአገልግሎት ማሳለጫ ቴክኖሎጂዎችን ለደንበኞች ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።

የኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተደራሽነትን ይበልጥ ለማሳደግ የሚረዳ ዘኔክሰስ የተሰኘ አገልግሎት በይፋ አስጀምሯል።

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፥ የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እውን ለማድረግ ኢትዮ ቴሌኮም ለቴሌኮምና ዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።

ባለፉት ስድስት ዓመታትም የአራተኛውና አምስተኛው ትውልድ ኔትወርክ አገልግሎት፣ ክላውድ፣ የቴሌብርና ዘመን ገበያን ጨምሮ ሥራ ላይ የዋሉ መሰረተ ልማቶች ትልቅ አቅም እየፈጠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የደንበኞችን ቁጥር ወደ 100 ሚሊዮን ለማድረስ ግብ መጣሉን ገልጸውም ከዚሁ ውስጥ 69 ሚሊዮን ደንበኞች የሞባይልና ብሮድባንድ ኢንተርኔት ተጠቃሚ ለማድረግ ስትራቴጂ ተነድፎ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል።


 

በኢትዮጵያ 85 ነጥብ 9 ሚሊዮን የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች እንዳሉ አመልክተው፤ ከእነዚህ ውስጥ 47 ሚሊዮኑ ብቻ ኢንተርኔትን እንደሚጠቀሙ አስታውቀዋል፡፡

ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም የመጠቀሚያ ስማርት መሳሪያዎች ዋጋ መወደድ ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ዘ ኔክሰስ የተሰኘ አገልግሎት ይፋ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የክላውድ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ የእጅ ስልኮች፣ ላፕቶፖች፣ ታብሌቶችና ወርክ ስቴሽኖች በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ማቅረቡን ተናግረዋል።


 

መሳሪያዎቹን የሚጠቀሙ ደንበኞች የኢትዮ ቴሌኮምን ክላውድ በቀጥታ በመጠቀም አገልግሎት ማግኘት የሚያስችላቸው መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ስማርት ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው ይህም የኢንተርኔት ተደራሽነትን በከፍተኛ ሁኔታ ያሻሽላል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት ግብርና፣ ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት፣ ትምህርትን ጨምሮ የተለያዩ መንግሥታዊ አገልግሎቶች በኢንተርኔት እንደሚሰጡ ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ ዘ ኔክሰስ አገልግሎት ወደ ስራ መግባት ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡

ዘኔክሰስ አገልግሎት ተቋማትን ተወዳዳሪ ለማድረግ እንዲሁም ቀልጣፋ ዘመናዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ እንዲያደርጉ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም