የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ከማስከበር ባለፈ በቀጣናው ተጽእኖ ፈጣሪ ሀገር በመገንባት ረገድ የመንግስት የዲፕሎማሲ ጥረት የሚደነቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ከማስከበር ባለፈ በቀጣናው ተጽእኖ ፈጣሪ ሀገር በመገንባት ረገድ የመንግስት የዲፕሎማሲ ጥረት የሚደነቅ ነው

ጭሮ፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ከማስከበር ባለፈ በቀጣናው ተጽእኖ ፈጣሪ ሀገር በመገንባት ረገድ የመንግስት የዲፕሎማሲ ጥረት የሚደነቅ መሆኑን በኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ አድገትና ብልጽግና እውን ለማድረግና ዓለም አቀፍ ተሰሚነቷን ለማጉላት በዲፕሎማሲው መስክ መንግስት በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።
በዚህ ረገድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በፖለቲካና ዲፕሎማሲው መስክ እንዲሁም ሀገራዊ የምጣኔ ሃብት እድገት እንዲያንሰራራ የሚያደርጉት ጥረት በብዙ መልኩ ይነሳል።
ከዙሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው በኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ከማስከበር ባለፈ በቀጣናው ተጽእኖ ፈጣሪ ሀገር በመገንባት ረገድ የመንግስት የዲፕሎማሲ ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በማጠናቀቅ፣ ሌሎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን የመገንባት ጅማሮና ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት በመንግስት የተያዘው ጠንካራ አቋም በሁላችንም የሚደገፍ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ አስተባባሪ የሆኑት ፈቃዱ ወርቁ፤ የመንግስት የዲፕሎማሲና የሀገር ሁለንተናዊ የልማት ጥረት የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የመልማት ፍላጎት እና ብሄራዊ ጥቅም በማንኛውም የውጭ ጫና የማይቀለበስ እንደሆነ የታየበት መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ተነጥላ ብትቆይም ከዚህ በኋላ ያለ ባህር በር መዝለቅ የማትችል መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስረዳት እየተሄደበት ያለው ርቀት ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።
የሀገርን ብሄራዊ ጥቅም ለማሟላት በሚያደርገው ጥረት የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው በዚህ ረገድ በጥናትና ምርምር እና በተያያዥ ስራዎች ለሀገር ብልጽግና የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ከመቸውም ግዜ በበለጠ ባሉት አማራጮች ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ የዘመቱት ሀገሪቱ ማንሰራራት በመጀመሯ በመሆኑ ይህንን በመረዳት ሁላችንም ለሀገራችን ብሄራዊ ጥቅም በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጋር በሚጻረር መልኩ በግብጽ በኩል የሚሰነዘሩ አሉታዊ እንቅስቃሴዎችን በጠንካራ ዲፕሎማሲ መመከት እንደሚገባም ነው የገለጹት።
በቅርቡ አንድ የግብጽ ከፍተኛ ባለስልጣን በሰጡት አስተያየት ላይ የውሀ እና ኢነርጂ ሚንስቴር ያወጣው መግለጫ ትክክለኛና የኢትዮጵያን አቋም በግልጽ ያሳየ መሆኑን በማከል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት ዲን ዘከርያ አብዱረህማን በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት የልማት እቅዶችን ከማሳካት ጎን ለጎን በባህር በር ላይ የያዘው ጽኑ አቋም የሚደገፍ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እየገነባች ባለው ከፍተኛ ኢኮኖሚ እና እየጨመረ ባለው የህዝብ ብዛት የተነሳ የባህር በር አልባ ሆና መቀጠል አትችልም፣ ለዚህም ለመንግስት ቁርጠኛ አቋም ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ ጠንካራ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በኩል ለሚሰነዘሩ አፍራሽ አጀንዳዎች መንግስት በዲፕሎማሲያዊ ጥብበ መመከቱን መቀጠል እንዳለበትም አስረድተዋል።