በውጭ ሀገራት ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር የነበረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ በስኬት ተጠናቋል - ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ ሀገራት ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር የነበረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ በስኬት ተጠናቋል - ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ)፦ በውጭ ሀገራት ከዳያስፖራው ማህበረሰብ ጋር የነበረው የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።
ኮሚሽኑ በተለያዩ የዓለም ሀገራት ሲያካሂድ የነበረውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ በመግለጫው እንዳሉት፤ በደቡብ አፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በካናዳ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ በስዊድንና እንግሊዝ የዳያስፖራ ወገኖች የተሳተፉበት መድረክ ተከናውኗል።
ተሳታፊዎች በመድረክ እንዲሁም በበይነ መረብ ሀሳባቸውን ማካፈላቸውንና አጀንዳዎቻቸውን ማቅረባቸውን ችለዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ለሀሳብ ልዩነትና መንስኤ ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች ተመካክረው በመለየት ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውንም ገልጸዋል።
አጀንዳ ከመስጠት ባለፈ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ የሚሳተፉ ተወካዮቻቸውን መምረጣቸውንም ነው የተናገሩት።
በመሆኑም መድረኮቹ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መብታቸውን ተጠቅመው በንቃት የተሳተፉባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።
በምክክሩ ያልተሳተፉ የዳያስፖራ አባላት በበይነ መረብ የሚሳተፉበት ዕድል እንዳለም ነው ያስታወቁት።
አጀንዳ ከማሰባሰብና ተወካዮችን ከማስመረጥ አኳያ የቀረው ትግራይ ክልል ላይ ብቻ መሆኑን በማንሳትም ለሂደቱ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር በቅርቡ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጋር ውይይቶች መደረጋቸውን በመጥቀስ።