ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት እያደረገች ያለው ጥረት በታሪካዊ ዳራ እና በዓለም አቀፍ ሕጎች መለኪያ ቅቡልና አሳማኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት እያደረገች ያለው ጥረት በታሪካዊ ዳራ እና በዓለም አቀፍ ሕጎች መለኪያ ቅቡልና አሳማኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት እያደረገች ያለው ጥረት በታሪካዊ ዳራ፣ ሕጋዊ ሠነዶች፣ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ እና ዓለም አቀፍ ሕጎች መለኪያ ቅቡልና አሳማኝ መሆኑን የሥነ-አመራርና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ጌትዬ ትርፌ(ዶ/ር) ገልጸዋል።
የባሕር በር ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን የኅልውና ጉዳይ መሆኑንም ነው በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-አመራርና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ጌትዬ ትርፌ(ዶ/ር) ለኢዜአ የተናገሩት።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት እያደረገች ያለው ጥረት በታሪካዊ ዳራ፣ ሕጋዊ ሠነዶች፣ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሕጎች መለኪያ ቅቡልና አሳማኝ መሆኑንም በአጽንኦት አንስተዋል።
እስካሁን ባለው ሂደትም በብዙ መመዘኛዎች ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዳለው መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
ለውጤታማነቱም ኢትዮጵያ ያላትን ሕጋዊ መሠረት፣ ታሪካዊና የሠነድ ማስረጃ በመጠቀም በሰላማዊ የዲፕሎማሲ ልዕልና ስልት ጥረቷን በይበልጥ ማጠናከር እንደሚጠበቅባትም መክረዋል።
ለዚህም አጋዡ መሣሪያ ለጎረቤት ሀገራት፣ ለአፍሪካ ኅብረት፣ ለምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን(ኢጋድ)፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማትና ተጽዕኖ ፈጣሪ የጋራ ዕድገት ደጋፊ ሀገራት የአቋሟን ትክክለኛነት በልኩ ማስገንዘብ መሆኑን አስረድተዋል።
የባሕር በር ለተሻለ ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ መሆኑን አስገንዝበው፤ ከሕግና ከሕዝብ ፍላጎት ውጭ በሆነ መንገድ እንድታጣ የተደረገችውን የባህር በር ማግኘት እንደሚገባትም ነው የተናገሩት።