በድንበር ተሻጋሪ ልማት አማካኝነት ሁሉን አቀፍ እድገት ለማረጋገጥ ይሰራል - ኢጋድ - ኢዜአ አማርኛ
በድንበር ተሻጋሪ ልማት አማካኝነት ሁሉን አቀፍ እድገት ለማረጋገጥ ይሰራል - ኢጋድ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ድንበር ተሻጋሪ ልማትን በማጠናከር የቀጣናዊ ትስስር እውን እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታወቀ።
በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ የሚገኘው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ዛሬ አራተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
ከዓመታዊው ስብሰባ ጎን ለጎን 26ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ስብሰባ የተከናወነ ሲሆን የድንበር ተቋራጭ ልማት ላይ ያተኮረ ውይይት በማድረግ የኢኒሼቲቩ ተሳታፊዎች የድንበር ተሻጋሪ ፍኖተ ካርታን አፅድቀዋል።
ፍኖተ ካርታውን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የፋይናንስ አሰራሮችም በመድረኩ ይፋ ሆነዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) ምክትል ዋና ፀሐፊ መሐመድ አብዲ ዋሬ ኢጋድ ድንበር ተሻጋሪ ልማት የቀጣናዊ አይበገሬነት፣ የኢኮኖሚ እድገትና የትስስር መሰረት እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ምክትል ዋና ፀሐፊው ከስብሰባው ጎን ለጎን የኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ የገንዘብ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት አመራሮች የሁለትዮሽ ውይይቶችን አደርገዋል።
ውይይቶቹ የኢጋድ የቀጣናዊ ትስስር እና የልማት ግቦችን የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ኢዜአ ከቀጣናዊ ተቋሙ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ እስከ ጥቅምት 8 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።