ቀጥታ፡

በአይ ኤም ኤፍ ኮታ ላይ የተደረገው የሃምሳ በመቶ ጭማሪ ለአለም አቀፍ ፋይናንሺያል ሴፍቲኔት መጠናከር አዎንታዊ ሚና አለው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 7/2018(ኢዜአ)፦ በአይ ኤም ኤፍ ኮታ ላይ የተደረገው የሃምሳ በመቶ ጭማሪ ለአለም አቀፍ ፋይናንሺያል ሴፍቲኔት መጠናከር አዎንታዊ ሚና እንዳለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ገለጹ።

ለአባል ሀገራት የሃብት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚረዳ አወንታዊ እርምጃ መሆኑን በመገንዘብም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተወሰደውን አርምጃ እንደሚቀበል አስታውቀዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዢው ይህን የተናገሩት እ.ኤ.አ ኦክቶበር 2025 ከአይ ኤም ኤፍ እና የዓለም ባንክ አመታዊ ስብሰባዎች ጎን ለጎን በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የAfrica Group III Constituency ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።


 

እንዲሁም የአይ ኤም ኤፍ ኮታ ማሻሻያ እንዲፋጠንም ገዢው ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ጥሪ አቅርበዋል።

ዶክተር እዮብ ተካልኝ በመድረኩ በሰጡት ማብራሪያ ይህ እርምጃ በአሁኑ ወቅት ያለውን የአለም ኢኮኖሚ ገጽታ በተሻለ መልኩ ከሚያንፀባርቅ ወቅታዊ እና ፍትሃዊ የኮታ ማስተካከያ(quota realignment) ጋር ማጣጣም አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኮታ ጭማሪውና ፈጣን አተገባበሩ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ጠቁመው፣ የኮታ ማስተካከያ አጣዳፊነት ግን እጅግ ከፍ ያለ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት ኢኮኖሚ አይ ኤም ኤፍ ከአለም አቀፍ የፋይናንስ ሴፍቲኔት ውስጥ አስተማማኝ የሆነ አጋር መሆኑን እና በኮታ ማሻሻያዎች ላይ የሚደረጉ መዘግየቶች ግን እነዚህ ሀገራት በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ አስተማማኝ ያልሆኑ ሁኔታዎችን ለመወጣት የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ሳያገኙ እንዲቀሩ እንደሚያደርጋቸው አስረድተዋል።

የታዳጊ አባል ሀገራት የኮታ ድርሻን መጠበቅ ላይ እየታየ ያለውን ስምምነት በማድነቅም አሁን ባለው ማዕቀፍ ታዳጊ ሀገራት ያላቸውን ዝቅተኛ ውክልና መፍታት አስፈላጊ እንደሆነ ገዢው በአጽንኦት አንስተዋል።

በመሆኑም ፍትሃዊ፣ ሚዛናዊና ሁሉን አቀፍ የሆነ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓትን ለማረጋገጥ ወደፊት በሚደረጉ የኮታ ማስተካከያዎች እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ዝቅጠኛ ውክልና ያላቸው ሀገራት ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም