የትጉዋ ኢትዮጵያ ሚና ድህነትን ለማጥፋት በሚደረግ ዓለም አቀፍ ርብርብ ውስጥ - ኢዜአ አማርኛ
የትጉዋ ኢትዮጵያ ሚና ድህነትን ለማጥፋት በሚደረግ ዓለም አቀፍ ርብርብ ውስጥ
ድህነትን ለማጥፋት በሚደረግ ዓለም አቀፋዊ ርብርብ ውስጥ ሀገራት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የተባበሩት መንግሥታት እ.አ.አ 1992 ባሳለፈው ውሳኔና ባጸደቀው አዋጅ አበክሮ ይጠይቃል።
የተባበሩት መንግሥታት ከላይ በተጠቀሰው ጊዜ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ በየዓመቱ እ.አ.አ ጥቅምት 17 ድህነትን ለማጥፋት የሚደረግ ጥረት የሚዘከርበት ቀን እንዲሆን ዓልሞ ዓለም አቀፍ ቀን አድርጎ አውጇል።
በዚህም መሠረት ሀገራት ከራሳቸው ሕዝብ ባለፈ የሌሎች ሀገራት ሕዝቦች ከድህነት እንዲወጡ አዋጭ ያሉትን ሁሉ ያደርጋሉ።
በእርግጥ የአንዳንዶቹ ድጋፍ በዕርዳታ ሥር የማቆየት እንጂ፤ ድህነትን ከሥሩ ነቅሎ ለመጣል የሚያስችል እንዳልሆነ ይስተዋላል። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ከድህነት ለመውጣት የምታደርገው ጥረት አርዓያነት ያለው ሆኖ ይነሳል።
በአጠቃላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሀገራት ድህነትን ለመቀነስ ብሎም ለማጥፋት በተደራጀ እና ዘላቂነት ባለው መንገድ ሲጓዙ የተባበሩት መንግሥታት ድህነትን ለማጥፋት ያስቀመጠውን ግብ መመለስ ተቻለ ማለት ነው።
በዛሬው ዕለትም የሚመለከታቸው ሀገራት ተወካዮች በተገኙበት የድህነት ቅነሳ ቀን በኒውዮርክ ከተማ ይካሄዳል። ቀኑን አስመልክቶ ኢትዮጵያ በዘርፉ እያከናወነች ያለችውን ሥራ በወፍ በረር እንቃኛለን።
አንዳንድ ሀገራት ስትራቴጂና ፖሊሲ ቀርጸው በራሳቸው ጥረት ከጊዜያዊ ዕርዳታ በመላቀቅ በዘላቂነት ድህነትን መቅረፍ የሚያስችል ሥራ ይሠራሉ። በዚህም የነበረባቸውን የድህነት መጠን የቀነሱ ብሎም ያመናመኑት ይኖራሉ።
ከዚህ አንጻር በተለይም ባለፉት 7 የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ ለሰው ተኮር ተግባራት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች። በዕርዳታ መኖርን በመፀየፍ ፍላጎቷን በራሷ አቅም ለመሸፈን የሚያስችላትን ሥራ በስኬት እያከናወነች እንደምትገኝም ይታወቃል።
ኢትዮጵያ እየሠራች ባለው ከፌደራል እስከ ታችኛው የመንግሥት መዋቅር በተሠናሠለና በተናበበ ሥራ አበረታች ውጤት እያስመዘገበች መሆኗ ይታመናል።
ተግባራዊ በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም ቀደም ሲል በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ ተይዘው ተግባራዊ ሲደረጉ በቆዩ ፕሮግራሞች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በማንሰራራት ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በዚህም መሠረት ከዕዳ ጫና በመላቀቅ በራስ አቅም ችግሮችን በመፍታት ከአግላይ የኢኮኖሚ ሥርዓት ወደ አሳታፊ እና ምቹ የኢኮኖሚ ምኅዳር በመሸጋገር፣ ከዝናብ ጥገኝነት ራስ ቻይ አምራች በመሆን፣ የማዕድን ጥሪትን ወደ ወሳኝ የሃብት ምንጭነት በመቀየር፣ የቱሪዝም ሃብትን ከመዳህ ጉዞ ወደ ጉልህ የዕድገት አንቀሳቃሽነት በማሳደግ፣ የሕዝብን አኗኗር ለመለወጥ እና ዘላቂ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል።
በ2017 የበጀት ዓመት፤ በግብርና ዘርፍ ፣ በኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም፣ የወርቅ ምርትና የሲሚንቶ ምርት እድገቶች እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ግኝት ያሳየው እድገት ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በተደረገ ጥረት፤ እስከ ሰኔ 2017 ድረስ የዋጋ ንረት ወደ 13 ነጥብ 9 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል። መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የቀጥታ ብድር ሳይወስድ የበጀት ዓመቱን ያጠናቀቀበት ጊዜም ነው።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በሰጠችው ልዩ ትኩረት አበረታች ውጤት ከማስመዝገብ ባለፈ በድህነት ቅነሳ ላይ ከፍተኛ ሚና ማበርከት ችላለች።
ከምግብ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ ስንዴን ከውጭ ማስገባት ያስቀረችው፤ ፍላጎቷን በራስ አቅም ከመሸፈን ያለፈ ምርት ማምረት የቻለችበትን አሠራር የዘረጋችው ኢትዮጵያ፤ ይህ ግብሯ በዓለም አቀፍ ተቋማት እና የተለያዩ ሀገራት በምሳሌነት እንድትወሰድ አስችለዋታል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጭነት ከሌማት ትሩፋት፣ የከተማ ግብርና፣ የበጋ መስኖ ልማት እንዲሁም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በየዘርፉ በትጋት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች በድህነት ቅነሳ ላይ ተጨባጭ አስተዋጽዖ እያበረከቱ ነው።
ተጠናቅቀው ትሩፋታቸውን ከሚለግሱ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ከ30 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጭ የሚደረግባቸው በኢነርጂ፣ በጋዝ፣ በማዳበሪያ፣ በቤት ልማት፣ በኒውክሌር ፕላንቴሽን እና በሌሎችም ዘርፎች እየተሠሩ ያሉ እና በቀጣይ የሚሠሩ ተግባራት ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት እያደረገች ያለውን ጉዞ ማርሽ ይቀይራሉ።
በተጨማሪም ትጉዋ ኢትየጵያ ዓለም ድህነትን ለማስወገድ በሚያደርገው ፍልሚያ የራሷን ጡብ እያኖረች መሆኗን ከላይ የተገለጹት እና ሌሎች ተግባሮቿ አስረጂ መሆናቸውን መረዳት ይቻላል።