ታማኝ ግብር ከፋዮች ለመዲናዋ ዕድገት፣ ልማትና ለትውልድ ግንባታ ደማቅ አሻራ በማኖር ላይ ናቸው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ታማኝ ግብር ከፋዮች ለመዲናዋ ዕድገት፣ ልማትና ለትውልድ ግንባታ ደማቅ አሻራ በማኖር ላይ ናቸው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፦ ታማኝ ግብር ከፋዮች ለመዲናዋ ዕድገት፣ ልማትና በትውልድ ግንባታ ስራ ላይ ደማቅ አሻራ በማኖር ላይ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና መርሐ ግብር እያካሄደ ይገኛል፡፡
በመርሐ ግብሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አፈ-ጉባኤ ቡዜና አልከድር፣ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት፤ ግብር ከፋዮች ለታማኝነታቸውና ለከተማቸው ልማት ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በከተማዋ የሚሰበሰበው ገቢ ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ መሆኑን ጠቁመው በ2010 በጀት ዓመት 33 ቢሊዮን ብር እንደነበር አስታውሰው በ2017 በጀት ዓመት ወደ 233 ቢሊዮን ብር ማደጉን ገልጸዋል፡፡
የገቢ ዕድገቱ የኢኮኖሚን መነቃቃትና ለውጥ በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመው በከተማዋ ጤናማ የገቢ አሰባሰብና የታክስ አስተዳደር ስርዓት በተሻለ መልኩ በመተግበር የተሰበሰበው ግብር ለከተማዋ ዕድገትና መዘመን እየዋለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተሰበሰበውን ግብር በታማኝነት ስራ ላይ በማዋል እያስመዘገብናቸው የምንገኛቸው ተጨባጭ ለውጦችና ልማቶች ግብር ከፋዩ የበለጠ ሃብት እንዲፈጥር የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል፡፡
የህዝቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ የሚገኙ እና አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ ያደረጉ የኮሪደርና የወንዝ ልማት ዳርቻ ልማቶችን ጨምሮ የተሰሩ የልማት ስራዎች በሚሰበሰበው ገቢ መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በርካታ የሥራ ዕድሎች መፈጠራቸውን ጠቁመው ኢኮኖሚው እየተነቃቃ፣ ከተማዋ በእጅጉ እየተለወጠችና ተቋማት እየዘመኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ መዳረሻ መሆን መጨመሩን አንስተው ከላይ የተገለጹት ለግብር ከፋዩ ስራ መስፋፋትና መላቅ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበርክቱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ግብር የፍትሐዊነት ማስፈኛ መሳሪያ መሆኑን ጠቁመው በየዓመቱ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ በማድረግ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች መደገፍ ማስቻሉን ጠቅሰው፥ በትምህርት ቤት ምገባም ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ እንዲመገቡ እያገዘን ነው ብለዋል፡፡
የግብር ከፋዮች ለከተማ እደገት ቀንዲል ናቸው ያሉት ከንቲባዋ ታማኝ ግብር ከፋዮች ለከተማዋ ዕድገት ግዴታቸውን በመወጣት ላይ መሆናቸውንም አክለዋል።
በዚህም በከተማዋ ዕድገትና ለውጥ እንዲሁም ለትውልድ እየተሰራ ባለው አጠቃላይ ስራ ዘመን ተሻጋሪ ደማቅ አሻራቸውን እያሳረፉ መሆኑን በአፅንኦት ገልጸዋል።