ቀጥታ፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ለጀመሩት ፕሮጀክት ድጋፍ ላደረጉ ለጋሾች የእራት ግብዣ አደረጉ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፦ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጀመሩት የአዳራሽ እና አካባቢን የማስዋብ ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ ላደረጉ ለጋሾችችና ባለሀብቶች የእራት ግብዣ አድርገዋል።

ፕሬዝደንቱ በነጩ ቤተ መንግስት የእራት ግብዣውን ያደረጉት አዲሱን የኋይት ሀውስ ታላቅ አዳራሽ እና አካባቢን የማስዋብ የ200 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት ለሚደግፉ ለጋሾች እና ባለሃብቶች መሆኑም ተገልጿል።

ግንባታው ባለፈው መስከረም ወር የተጀመረውና 90 ሺህ ስኩዌር ጫማ(8 ሺህ 361 ካሬ ሜትር) አዳራሽ በ10 ሺዎች የሚቀጠሩ እንግዶችን ያስተናግዳልም ተብሏል።

በዚህ ወቅት ፕሬዝዳንቱ አንደገለጹት ፕሮጀክቱ አሜሪካን በዓለም መድረክ በተሻለ ሁኔታ እንዲወክል የሚያስችል ነው።

አሁን ላይ ያለው መሠረተ ልማት መሪዎችን ለመቀበል እና ለማነጋገር ብሎም የተለያዩ ሁነቶችን ለማስተናገድ ምቹ አለመሆኑንም አንስተዋል።

የታላቁ አዳራሽ ፕሮጀክት ከኋይት ሀውስ ንድፍ ጋር የሚስማማ ተደርጎ እንደሚገነባ ገልጸው፤ ለፕሮጀክቱ ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙ ባለሃብቶች እና ኩባንያዎችንም አመስግነዋል።

የአሜሪካው የመከላከያና አይሮስፔስ ካምፓኔ ፣የማይክሮሶፍት፣ የሜታ፣ የጉግል፣ የአማዞን እና የቲ-ሞባይል ተወካዮችን ጨምሮ በርካታ የክሪፕቶ ስራ ፈጣሪዎች እና ባለሃብቶች መገኘታቸውን ሲኤን ኤን ዘግቦታል።

ዛሬ ላይ ፕሬዝዳንቱ የጀመሩት ‘የሌጋሲ ዲነር’ ስራ ቀደም ባሉት ዓመታት በአዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በሚል መጀመሩ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለፕሮጀክቶቹ ትግበራ ገንዘቡን በ“ገበታ ለሸገር” የእራት ምሽት ፕሮግራም በማዘጋጀት ሀገር ወዳድ ባለሀብቶችም በአምስት ሚሊዮን ብር ገበታውን በመቋደስ አሻራቸውን አኑረዋል።

ይህ እንቅስቃሴም አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ ከማድረግ ጀምሮ ዜጎች እና ባለሀብቶች የነቃ ተሳትፎ ባደረጉበት የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች ከአዲስ አበባ ውጪም ማለትም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኮይሻ፣ በአማራ ክልል ጎርጎራ፣ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ወንጪን ማልማት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም