ፍትሃዊ እና ሁሉን አሳታፊ የባለብዙ ወገን የፋይናንስ ስርዓት የመፍጠር ጉዳይ ልዩ ትኩረት ይሻል- የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
ፍትሃዊ እና ሁሉን አሳታፊ የባለብዙ ወገን የፋይናንስ ስርዓት የመፍጠር ጉዳይ ልዩ ትኩረት ይሻል- የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፦ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ፍትሃዊ ውክልናና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የባለብዙ ወገን የፋይናንስ ስርዓት ለመፍጠር በትኩረት መስራት እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ገለጹ።
በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ የሚገኘው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ከዓመታዊ ስብሰባው ጎን ለጎን በተካሄደው የ24 ሀገራት የበይነ መንግስታት ቡድን(G-24) 114ኛው የሚኒስትሮች እና የብሄራዊ ባንክ ገዥዎች ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል።
ቡድን 24 በአፍሪካ፣ እስያ፣ ላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያን በማደግ ላይ የሚገኙ 24 ሀገራትን ያቀፈ የሞኒተሪ እና የልማት ጉዳዮች የትብብብር ማዕቀፍ ነው።
የወቅቱ ሊቀ መንበር አርጀንቲና በሊቀ መንበርነት የመራችው ስብሰባ የእድገትን አቅምን መጠቀም በሚያስችሉ መዋቅራዊ የትራንስፎርሜሽን ፖሊሲዎች ላይ ያተኮረ ነው።
በስብሰባው ላይ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ፣ የዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቢርድ እና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ኢሲኤ) የፕሮግራም ዘርፍ ምክትል ዋና ፀሐፊ እና ዋና ኢኮኖሚስት ሃናን ሞርሲ ተገኝተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት እውነተኛ ድምጻቸው የሚሰማበትና የፋይናንስ ተደራሽነታቸውን የሚያሳድግ ፍትሃዊ፣ የተሻለ የባለብዙ ወገን ስርዓት መፈጠር እንዳለበት አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ የቡድን 24 በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የእዳ ሽግሽግ (G20 Common Framework debt treatment) ስር ተገማች እና ወቅቱን ያማከለ የእዳ ማሸጋሸጊያ አሰራሮች ሊኖሩ ይገባል በሚል ላወጣው መግለጫ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
አቶ አሕመድ በንግግራቸው በረጅም ጊዜ የሚከፈሉና አነስተኛ ወለድ ያላቸው እንዲሁም ተለዋጭ የአከፋፈል ሁኔታዎች ያላቸው ብድሮች፣ የባለብዙ ወገን ትብብርን በአዲስ መልክ ማደስ እና አጋርነትን ማጎልበት ወሳኝ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት የቀውስ ወቅት ምላሽና ከረጅም ጊዜ ልማት ጋር የሚጣጣም የዓለም ስርዓት መፍጠር እንደሚገባም አመልክተዋል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ እና የዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቢርድ በቡድን 24 እየተደረጉ ያሉ የሪፎርም ስራዎችን ያደነቁ ሲሆን የፋይናንስ ተቋማቱ ከአባል ሀገራቱ ጋር ጠንካራ የፕሮግራም ትስስር ለመፍጠር ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል።
የባንኮቹ ከፍተኛ አመራሮች የቡድን 24 አባል ሀገራት የፋይናንስ መረጋጋትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ለዘላቂና ሁሉን አቀፍ እድገት መሰረት የሚጥል ስራ እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።
የባለብዙወገን የልማት ባንኮች እና የግል አበዳሪዎች የቡድን 24 ጥረቶችን እንዲደግፉ ጥሪ ማቅረባቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ የላከው መረጃ ያመለክታል።