ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መድረኮች የአፍሪካን መሪነት ለማሳደግ ቁርጠኛ ናት- ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መድረኮች የአፍሪካን መሪነት ለማሳደግ ቁርጠኛ ናት- ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መድረኮች የአፍሪካን መሪነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የእውቅና እና የምስጋና መርኃ ግብር አካሂዷል።
በመርኃ ግብሩ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፣ የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያሥላሴ፣ ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ተገኝተዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ምላሽ ለመስጠት ያለንን ቁርጠኝነት ያረጋገጥንበት ነው ብለዋል።
ጉባዔው አፍሪካውያን ለአየር ንብረት ለውጥ ተጨባጭ መፍትሔዎችን በመውሰድ ግንባር ቀደም መሆናቸውን ለዓለም በማሳየት ስኬታማ መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ለጋራ ችግሮች በጋራ ምላሽ ለመስጠት አቅማቸውን ያጠናከሩበት እንደሆነ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ስኬት ተጠቅሞ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መድረኮች የአፍሪካን መሪነት ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።