ቀጥታ፡

በምስራቅ ቦረና ዞን ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኽር ሰብሎች በዘር ተሸፍኗል

ነገሌ ቦረና፤ ጥቅምት 6/2018 (ኢዜአ) ፡-በምስራቅ ቦረና ዞን ከ100 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኽር  ሰብሎች በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ቦነያ ሁቃ በዞኑ የመኽር አዝመራ ከመስከረም ወር እንደሚጀምር አንስተው ለዚህም 126 ሺህ 434 ሄክታር መሬት ታርሶ  ወደ ዘር መገባቱን አስታውቀዋል፡፡ 

ለዘር ከተዘጋጀውም መሬትም እስካሁን በስንዴ፣ በጤፍ፣ በሽምብራ በቦለቄና በቆሎ የምርጥ ዘር አይነቶች 101 ሺህ 270 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡

በመኽር አዝመራው 112 ሺህ 487 የዞኑ ከፊል አርብቶ አደሮች መሳተፋቸውን ገልጸው በዘር ከሚሸፈነው መሬትም 1 ሚሊዮን 656 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ  ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ 

በጽህፈት ቤቱ የመካናይዜሽን ግብአት አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ አብዱረሂም አብዱረህማን በዞኑ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ  አዳዲስ የግብርና አሰራሮች  እየተተገበሩ ነው ብለዋል፡፡

ምርታማነቱን ለመጨመር የኩታ ገጠም አስተራረስ ትግበራን ጨምሮ በትራክተር የሚታረስና የግብአት አጠቃቀም ላይ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡

በግብአት አቅርቦትም  4 ሺህ ኩንታል የምርጥ ዘርና ከ36 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ መቅረቡን አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ ሊበን ወረዳ የጎቢቻ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ቦነያ አሬሮ፣ ሁለት  ሄክታር መሬታቸውን  በስንዴ፣ በቦለቄና በጤፍ ምርጥ ዘር ማልማታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ምርታማነታቸውን ለማሳደግም ማዳበሪያና ምርጥ ዘርን በመጠቀም ከ30 ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

ወጣት ሁሴን አብዱላሂ በበኩሉ በመኽር አዝመራ ሁለት ሄክታር መሬቱን ደጋግሞ በማረስ በምርጥ ዘር  የመሸፈን ተግባር ላይ መገባቱን ጠቁሟል፡፡

ለዚህም  የስንዴ ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ በመጠቀም በኩታ ገጠም በማልማት መሆኑን ተናግረዋል።

በዘር ከሸፈነው መሬትም  ከ40 ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ለመሰብሰብ  ማቀዱን አክሏል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም