ታማኝ ግብር ከፋዮች አዲስ አበባ እንደገና እንድትሰራ አድርገዋል - አቶ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
ታማኝ ግብር ከፋዮች አዲስ አበባ እንደገና እንድትሰራ አድርገዋል - አቶ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፦ ታማኝ ግብር ከፋዮች አዲስ አበባ ለአፍሪካ ከተሞች ምሳሌ እንድትሆንና እንደገና እንድትሰራ በማድረግ የላቀ ሚና መወጣታቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና መርሐ ግብር አካሂዷል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ መንግሥት ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በጥራት እየተገበረ ይገኛል ብለዋል።
ለዚህም የገቢ ሰብሳቢ ተቋማት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት በቂ ገቢ ለመሰብሰብና ሀገራዊ የልማት ዕቅዶችን ለማሳካት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የፌደራል መንግሥትም ሆነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢ የመሰብሰብ አቅማቸው እያደገ ነው ያሉት አቶ አገኘሁ፥ በዚህም የማህበረሰቡን ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት እያረጋገጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ የታማኝ ግብር ከፋዮች ሚና ወሳኝ መሆኑን በማንሳት፥ በከተሞች እድገት፣ በወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራና የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ሌሎች ዘርፎች ጉልህ ስኬቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል።
የአዲስ አበባን አዳጊ ፍላጎት በበቂ ደረጃ ለማሟላት የገቢ ሰብሳቢ ተቋማትና ግብር ከፋዮች ይበልጥ ተቀናጅቶ መስራትና ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በገቢ ዘርፍ ሪፎርሙ የታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ስርዓትን በማሻሻል የሚሰበሰበው ገቢ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፥ ታማኝ ግብር ከፋዮች ለሀገርና ለከተማዋ ልማት ላበረከቱት አስተዋፅኦ አመስግነዋል።
በአዲስ አበባ የሚታየው ሁለንተናዊ ለውጥ ያለታማኝ ግብር ከፋዮች ይሳካል ተብሎ እንደማይታሰብ በመጠቆም፥ ግብር ከፋዮች አዲስ አበባ ከተማ እንደገና እንድትሰራ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ለከተማዋ ዕድገት በተለይም አዲስ አበባን የአፍሪካ ከተሞች ምሳሌ እንድትሆን እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
የመዲናዋ ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አበክሮ መስራት እንደሚገባ በግልፅ፥ የግብር ከፋዩን መሰረታዊ አገልግሎትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በየጊዜው እየፈተሹ መፍትሄ መስጠትን የትኩረት ማዕከል ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።