ቀጥታ፡

ለፍልሰተኞች የሚሰጡ ድጋፎችና ምላሾችን በስትራቴጂ ዕቅድ በመምራት የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ይሰራል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ለፍልሰተኞች የሚሰጡ ድጋፎችና ምላሾችን በስትራቴጂ ዕቅድ በመምራት የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሰራ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ገለጹ።

የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎች ህጋዊ በሆነ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር እንዲሄዱ እንዲሁም በሀገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል፡፡

በዚህም ዜጎች በሀገራቸው እንዲሰሩ፣ ህጋዊና ደህንነቱ የተረጋገጠ የፍልሰት አስተዳደር ለመዘርጋትና ከፍልሰት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ እቅድ ይፋ ተደርጓል።


 

ስትራቴጂክ ዕቅዱ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ መንግስትና በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ትብብር ነው፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ለፍልሰተኞች ምላሽና ድጋፍ የሚሰጡ ማዕከላት እየተቋቋሙና ፍልሰተኞችን የሚያካትቱ ማህበረሰብ አቀፍ መርኃ ግብሮች እየተከናወኑ ናቸው።

በተለይም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ዜጎች ለበርካታ ችግሮች እንደሚጋለጡ አንስተው፤ ስትራቴጂ ዕቅዱ ችግሮቹን ለማቃለል እንደሚረዳ አመልክተዋል።

ስትራቴጂክ እቅዱ ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው የሚለወጡበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱበትን መንገድ ማመቻቸት፣ የፍልሰተኞችን ህይወትና ደህንነት መጠበቅና ሌሎች ሁኔታዎችንም ማካተቱን ተናግረዋል።

መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን መከላከል፣ ከፍልሰት ተመላሾችን ከቤተሰብ ጋር ማገናኘት፣ በውጭ የሚገኙ ዜጎችን ደህንነት በማስጠበቅ ውጤታማ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

በፍትህ ሚኒስቴር የብሄራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ሴክሬታሪያት ሃላፊ አብርሃም አያሌው በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።

የሀገሪቱን የፍልሰት አስተዳደር ለማጠናከር፣ ተጠያቂነትን ለማሳደግ፣ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የሚረዱ የሪፎርምና የአቅም ግንባታ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቢባቱ ዋኔ እንደገለጹት፤ ስትራቴጂክ ዕቅዱ በዋናነት መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት የዜጎች ህይወት እንዳይጠፋና መደበኛ ፍልሰትን ለመደገፍ ያግዛል።

የፍልሰተኞች ጉዳይ የጋራ ሀላፊነት በመሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት መስራታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም