ስማርት ድሬዳዋን ዕውን ለማድረግ እና መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በስፋት ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ስማርት ድሬዳዋን ዕውን ለማድረግ እና መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በስፋት ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ ነው

ድሬዳዋ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፡- ስማርት ድሬዳዋን ዕውን ለማድረግ እና መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በጥራትና በስፋት ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።
በድሬዳዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለሚገነባው የአይ ሲ ቲ ትምህርትና ስልጠና ልህቀት ማዕከል ዛሬ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።
የመሠረት ድንጋዩን ያስቀመጡት ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአስተዳደሩ ምክርቤት የመንግስት ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ እና የካቢኔ አባላት ናቸው።
በዚህ ወቅት ከንቲባው እንደገለጹት፤ ማዕከሉ ስማርት ድሬዳዋን ዕውን ለማድረግ ለሚከናወነው ሥራ ወሳኝ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
የልህቀት ማዕከሉ በተጨማሪም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በጥራትና በስፋት ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት መሠረታዊ ሚና እንደሚኖረው ነው ያመለከቱት።
ባለ አምስት ወለል የሚሆነው የልቀት ማዕከል ግንባታ ሥራ በተያዘለት የ14 ወራት ጊዜ ውስጥ በጥራትና በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአስተዳደሩ ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው ለድሬዳዋ ዲጂታል የለውጥ ጉዞ ዕውን መሆንና በዘርፉ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ ለመገንባት ማዕከሉ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የድሬዳዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ሰላሃዲን አብዱልሃሚድ በበኩላቸው፤ ማዕከሉ በውስጡ 42 ክፍሎች እንደሚኖሩት ገልጸዋል።
የኮምፒውተር ላቦራቶሪ፣ የምርምርና የመማሪያ ክፍሎች፣ እንዲሁም የዲዛይን ስቱዲዮ፣ የኮንፍረንስ እና የዲጂታል ቤተ-መጻህፍትን እንደሚያካትም ተመላክቷል።