ኢትዮ ቴሌኮም የኢንተርኔት አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የሚረዳ ዘ ኔክሰስ የተሰኘ አገልግሎት ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ ቴሌኮም የኢንተርኔት አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የሚረዳ ዘ ኔክሰስ የተሰኘ አገልግሎት ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮ ቴሌኮም የኢንተርኔት አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የሚረዳ ዘ ኔክሰስ የተሰኘ አገልግሎት ይፋ አድርጓል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ አገልግሎቱን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በዚሁ ወቅት፤ በኢትዮጵያ 85 ነጥብ 9 ሚሊዮን የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች እንዳሉ አመልክተው፤ ከእነዚህ ውስጥ 47 ሚሊዮኑ ብቻ ኢንተርኔት እንደሚጠቀም አስታውቀዋል፡፡
ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም የመጠቀሚያ ዲቫይሶች (መሳሪያዎች) ዋጋ መወደድ ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ዘ ኔክሰስ የተሰኘ አገልግሎት ይፋ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የክላውድ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ ፊውቸር ፎኖች(የእጅ ስልኮች) ላፕቶፖች፣ ታብሌቶችና ዴስክ ቶፕ ኮምፒዩተሮች በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ ማቅረቡን ገልጸዋል።
መሳሪያዎቹን የሚጠቀሙ ደንበኞች የኢትዮ ቴሌኮምን ክላውድ በቀጥታ በመጠቀም የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት የሚያስችላቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ግብርና፣ ዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት፣ ትምህርትን ጨምሮ የተለያዩ መንግሥታዊ አገልግሎቶች በኢንተርኔት እንደሚሰጡ ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ ዘ ኔክስ አገልግሎት ወደ ስራ መግባት ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡