የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘት ሀገርን ያኮራና ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ ነው - ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘት ሀገርን ያኮራና ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ ነው - ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር በምርጥ የዘላቂ የደን ልማት አያያዝና አጠቃቀም ዘርፍ ከዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ዕውቅና ማግኘቱ ሀገርን ያኮራና ለበለጠ ሥራ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት በጣሊያን ሮም ባካሄደው የዓለም የምግብ ጉባዔ ላይ ለኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ምርጥ የዘላቂ የደን ልማት አያያዝና አጠቃቀም በሚል ዘርፍ ዕወቅና ሰጥቷል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ፀሐፊ ፋኖሴ መኮንን በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በዚሁ ወቅት ድርጅቱ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር እያከናወነቻቸው ላሉ ተግባራት የሰጠው ዕውቅና ለህዝቡ ትልቅ የሞራል ስንቅ የሚሆንና ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በ2011 ዓ.ም ይፋ መደረጉን አስታውሰው፤ በስምንት ዓመታት ውስጥ በሁለት ምዕራፍ 50 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እስካሁን 48 ቢሊዮን ችግኝ ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት።
ከመደበኛው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በተጨማሪ የአንድ ጀምበር የተከላ መርሃ ግብርም ዜጎች ለአንድ የጋራ ዓላማ የቆሙበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
"በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብም በ2017 ዓ.ም ክረምት ወቅት በተካሄደው የአንድ ጀምበር ችግኝ ተከላ ከ29 ሚሊዮን ህዝብ በላይ በነቂስ ወጥቶ ከ714 ሚሊዮን ችግኝ በላይ መትከሉን ለአብነት አንስተዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ ከችግኝ ተከላ በላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ መርሃ-ግብሩ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ለዘላቂ የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ ለስራ ዕድል ፈጠራና ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ቅነሳ የጎላ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
በየዓመቱ እየተተከሉ ያሉ በርካታ ችግኞች አሁን ላይ ውጤታቸው በግልጽ መታየት መጀመሩንም ጨምረው አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት(ፋኦ) የተሰጣት ዕውቅናም ሀገርን ያኮራ፣ ዜጎቿንና ሌሎች ሀገራትን ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳ መሆኑን ተናግረዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ ዕወቅናውን ትናንት በተቀበሉበት ወቅት ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋኗን ማሳደጓን አንስተዋል።
ይህ ስኬት በመሪ ግልጽ ራዕይና ተግባር፣ በህዝብ ተሳትፎ የመጣና ተስፋን ያለመለመ መሆኑንም ነው የገለጹት።