ቀጥታ፡

ማዕከሉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ብቁ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ባለሙያዎችን ማፍራት ያስችላል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ብቁ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ባለሙያዎችን ለማፍራት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል ማስጀመሪያ መርኃ ግብር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ተካሂዷል።


 

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን(ዶ/ር) የመገናኛ ብዙኃን ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ብሔራዊ ጥቅም መከበር የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

የልህቀት ማዕከሉ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ ጋዜጠኝነትን የተካነ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ለማፍራት ያግዛል ብለዋል፡፡

በብቁ የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ የተደራጀ መሆኑን ገልጸው፤ ከፖሊሲ አውጪዎችና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ነው ያስታወቁት፡፡

የምርጫ ጋዜጠኝነት ሥልጠና በቅርቡ እንደሚጀምር በማንሳት፤ ማዕከሉ በውሃ፣ በማዕድን፣ በአየር ንብረት፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በአቪየሽንና በሌሎችም ዘርፎች ስልጠና እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡


 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ጋዜጠኝነት ከሙያ ዕድገት ጋር የተጣጣመ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ፣ ብልጽግናን ዕውን ለማድረግ፣ የወል ትርክትን ለመገንባትና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ ግልጽ ሀሳብ፣ ብቁ ተቋማትና ብቁ ባለሙያ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የጋዜጠኝነት ሙያን በማሳደግ ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበሪያ መሳሪያ ለማድረግ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠው መደበኛ ትምህርት ብቻ በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ሙያን ለማዳበርና የመገናኛ ብዙኃንን አቅም ለማጎልበት ወቅቱን የዋጁ ስልጠናዎችና የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የሚሰጥበት አሰራር ዘርግቷል ብለዋል፡፡


 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር እና አማካሪ አንተነህ ጸጋዬ(ዶ/ር) እንዳሉት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በነጻነት እንዲሰሩ የሚያስችሉ በርካታ የፖሊሲና የህግ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ መገናኛ ብዙኃኑ አፋኝ ህጎች ተሻሽለው ምቹ የሥራ ምህዳር ቢፈጠርም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የሚጠበቅባቸውን ያህል አልተወጡም ብለዋል፡፡

በመሆኑም ችግሩን ለመፍታት የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል በሙያዊ አቅም ግንባታ አንደኛው የመፍትሔ አማራጭ ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም