በምዕራብ ጎንደር ዞን የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ከዘርፉ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ጎንደር ዞን የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ከዘርፉ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ጥረት እየተደረገ ነው

ገንዳውሃ ፤ ጥቅምት 6/2018 (ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጎልበት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ።
መምሪያው ከገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር "ቱሪዝም ለዘላቂ ለውጥ" በሚል መሪ ሃሳብ ዘርፉን ለማነቃቃት ያለመ የባሕልና ቱሪዝም ፌስቲቫል ዝግጅት ዛሬ አካሂዷል።
በዝግጅቱ ላይ የመምሪያው ኃላፊ አስያ ዑመር እንዳሉት፤ በዞኑ የአልጣሽና ጎደቤ ብሔራዊ ፓርኮች፣ የማሕበረ ስላሴ አንድነት ገዳም ጥብቅ ስፍራና ሌሎች የመስህብ ሃብቶች ይገኛሉ።
እነዚህን የቱሪስት መዳረሻዎች በማልማትና በማስተዋወቅ እንዲሁም የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን አቅም በማሳደግ ከዘርፉ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው ፌስቲቫልም የአካባቢውን ባህላዊ ምግቦች ለቱሪስቶች በማስተዋወቅ ለስራ እድል ፈጠራ የሚውሉበትን አሰራር ለማስፋት ያለመ ዝግጅት መካሄዱን ጠቁመዋል።
ዝግጅቱ የአካባቢውን ባህላዊ ክዋኔዎች ጭምር በማስተዋወቅ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን አስረድተዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የምዕራብ ጎንደር ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ጌታቸው አስበው በበኩላቸው፤ የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ የብልፅግና ጉዞ መሰረት ነው ብለዋል።
በመሆኑም ዞኑ ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሀብት ለማልማት ከሕብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የቱሪዝም አቅምን በአግባቡ ወደ ውጤት ለመቀየርም ሕዝቡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ተሳትፎውን ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።
ከዝግጅቱ ተሳታፊዎች መካከል ከመተማ ወረዳ የመጡት አድና አይጠገብ በሰጡት አስተያየት፤ የቱሪዝም ፀጋን በማልማት ለኢኮሚያዊ ጥቅም ለማዋልና የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ሌላኛው ተሳታፊ የገንዳውሃ ከተማ ነዋሪ አየነው አለነ ፤ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን በማልማትና ቅርሶችን በመጠበቅ በሚደረገው ሂደት በመሳተፍ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።