ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል ብሔራዊ ጥቅምን ያማከለ የሚዲያ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና አለው - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል ብሔራዊ ጥቅምን ያማከለ የሚዲያ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና እንዳለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ የሚዲያ ልህቀት ማዕከል ማስጀመሪያ መርኃ ግብር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ተከናውኗል።


 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መገናኛ ብዙሃን ትኩስና ወቅታዊ መረጃዎችን በማቅረብ ለሰላም ግንባታና ለህብረተሰብ አመለካከት ለውጥ የማይተካ ሚና አላቸው።

መንግሥት ህጎችንና አሠራሮችን በማሻሻል የመገናኛ ብዙሃንን በአይነትና በቁጥር ማስፋት መቻሉን ገልጸዋል።

በዚህም መገናኛ ብዙሃኑ ታላላቅ ሀገራዊ ጉዳዮች በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝቡን በንቃት በማሳተፍ፤ ሀገራዊ ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በማድረግ ገንቢ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልፅግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም በሰላም፣ በልማት፣ በሕብረ ብሔራዊ አንድነትና ሀገር ግንባታ ላይ ገንቢ ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ የሚዲያ አውድ ተቀይሯል ያሉት አፈጉባኤው፤ የዲጂታል ጋዜጠኝነት መስፋፋት የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርን የጣሱ አካላት ግን ተገቢ ያልሆነ ይዘት እንዲያሰራጩ በር መክፈቱን ገልጸዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ሃሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን በማሰራጨት በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል ብለዋል፡፡


 

በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ሥነ ምግባርን በጠበቀ መልኩ የሀገርና የህዝብ ጥቅምን የማስከበር ተልዕኳቸውን እንዲወጡ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል የጋዜጠኝነት ሙያ ስነ-ምግባር የተላበሰና ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ የሚዲያ ስርዓት ለመፍጠር፣ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ የሚዲያ ተደራሽነትን ለማስፋት ያግዛል ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ለማዕከሉ እድገትና ለመገናኛ ብዙሃን ምህዳር መስፋት አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም