ቀጥታ፡

መገናኛ ብዙኃን ሕብረ ብሔራዊ አንድነትንና ሀገራዊ ብልጽግናን የማስረጽ ተልዕኳቸውን መወጣት አለባቸው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙኃን ሕብረ ብሔራዊ አንድነትንና ሀገራዊ ብልጽግናን የማስረጽ ተልዕኳቸውን መወጣት እንዳለባቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አስገነዘቡ፡፡

የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል ማስጀመሪያ መርኃ ግብር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ተካሂዷል።


 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በሀገራችን ያለው ጋዜጠኝነት ኢትዮጵያን መምሰል አለበት።

በኢትዮጵያ ያሉ የግልም ይሁኑ የህዝብ ወይም የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን በአራት ጉዳዮች ላይ ልዩነት ሊኖራቸው አይገባም ብለዋል።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ በማንኛውም መገናኛ ብዙሃን የሚሰራ ጋዜጠኛ ሊረሳው የማይገባ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያጠናክሩ፣ የህዝብን ትብብርና አንድነት የሚያሳዩ መሆን አለባቸው ብለዋል።

የወል ትርክትን መገንባት እና ኢትዮጵያ መበልጸግ አለባት የሚለውን ሀገራዊ የብልጽግና ዕሳቤ ታሳቢ አድርገው መስራት እንዳለባቸውም አፅንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን መገናኛ ብዙኃንን ለመደገፍና ለማብቃት ያደረገው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ፈቃድ የወሰዱ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያን መምሰል አለባቸው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን ማበልጸግ ዘመናትን የተሻገረ የልሂቃን ዕሳቤ መሆኑን ያነሱት አማካሪ ሚኒስትሩ፤ ጋዜጠኝነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠበቅ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

መገናኛ ብዙኃን በሁሉም ህብረተሰብ ዘንድ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትና ብልጽግናን የማስረጽ ተልዕኳቸውን መወጣት እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡

ብሔራዊ ጥቅምን፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ የወል ትርክትና ሀገራዊ ብልፅግናን በማስረጽ ተልዕኳቸው ላይ ልዩነት ሊኖራቸው አይገባም ብለዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል የመገናኛ ብዙኃን ዘርፉ የሚጠይቀውን ስልት፣ ፈጠራና ብቃት ለማሟላት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡

ጋዜጠኝነት ተምሮ የሚገባበት ብቻ ሳይሆን በየጊዜው ብቃቱ የሚለካበት፣ የሙያ ፈቃድ የሚሰጥበትና የሚታደስበት መሆን አለበት ብለዋል፡፡

በመርኃ ግብሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም