የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው - ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው - ሚኒስቴሩ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፦ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ የሚገኘው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያሳደገ መምጣቱን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ ገለጹ።
ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደገለጹት ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግሥት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በተጠናከረ ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲመራ በማድረጉ አበረታች ውጤቶች እንዲታይበት አስችሏል፡፡
ይህም የማኅበረሰቡን ችግር ከመፍታት ባለፈ የሀገር ልማትን በማፋጠን ሂደት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እርስ በእርስ የመተባበር፣ የመተጋገዝና የአብሮነት እሴት እንዲዳብር አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በ2017 ዓ.ም በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የቤት እድሳትና ግንባታ፣ የአረንጓዴ ዐሻራና የአካባቢ ልማት ስራዎች እንዲሁም ትምህርታዊ ስልጠናዎች ብሎም የደም ልገሳ ተግባራት ተከናውነው ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።
ወጣቶች እና ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ባሳዩት የእኔነት ስሜትና ርብርብ አቅመ ደካማ ዜጎችንና አረጋውያንን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ባህል ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች በበጋው ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡
በመዲናዋ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግል የቆየው ባህረዲን ኩራቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትልቅ የህሊና እረፍት የሚሰጠው በደስታ የሚያከናውነው ተግባር እንደሆነ ተናግሯል።
በትራፊክ አስተናባሪነት፣ በደም ልገሳና በሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በመሳተፍ ህብረተሰቡን ሲያገለግል መቆየቱን ጠቅሶ ይህን ተግባሩን በቀጣይም እንደሚያጠናክር ገልጿል።
ሌላኛዋ በጎ ፈቃደኛ ወጣት የማሪያምወርቅ አሰፋ በበኩሏ፤ በከተማዋ በአቅመ ደካሞች የቤት እድሳትና በትራፊክ አስተናባሪነት እየተሳተፈች መሆኑን ገልጻለች።
በአሁኑ ወቅትም ትምህርት ቤቶች የተከፈቱበት ወቅት እንደመሆኑ ተማሪዎች ለትራፊክ አደጋ ተጋላጭ እንዳይሆኑ የበኩሏን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጣለች።
ወጣቶች ያለንን እውቀትና ልምድ ተጠቅመን በበጎ ፈቃድ ያለንን ተሳትፎ ልናጎለብት ይገባል ስትል ጥሪዋን አቅርባለች።
በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቤታቸው የታደሰላቸው አቶ ሳሙኤል አበበ ለበርካታ ዓመታት ዝናብና ፍሳሽ በሚያስገባ ቤት መኖራቸውን አስታውሰው ክረምት በመጣ ቁጥር ከአሁን አሁን ይሄ ቤት አንድ ነገር ሆነ እያልኩ በሀሳብና በጭንቀት አሳልፍ ነበር ብለዋል።
ባላቸው የአቅም ውስንነት ሳቢያ ቤተሰብን ከማስተዳደር አልፎ ቤት ለማደስ አቅም እንዳልነበራቸው ገልጸው በአሁኑ ወቅት ደግሞ በበጎ ፈቃደኞች ቤታቸው በመሰራቱ የተሰማቸውን ልዩ ደስታ ለኢዜአ አጋርተዋል።
ለሰው ልጅ ለመኖር ምቹ ሁኔታ በሌለበት ቤት ውስጥ ከአንድ ልጃቸው ጋር ህይወትን ሲገፉ እንደነበረ የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ሸዋዬ ከተማ ናቸው።
በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቀና ልብ ባላቸው በጎ ፈቃደኞች ቤታቸው በመታደሱ ልጃቸውም እሳቸውም በተመቸ ሁኔታ እየኖሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ አያይዘውም የበጎ ፈቃድ ስራ ለእነሱ መልካም ዕድልን ይዞ እንደመጣ ሁሉ ሌሎችም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ አረጋውያንና አቅመ ደካሞችን የማገዝ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።