ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት የሥራ ዕድል ፈጠራ ውጤታማ ተግባር እያከናወነች ትገኛለች

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል በአፍሪካ ግንባር ቀደም የሆነ ተግባር እያከናወነች መሆኑ ተገለጸ።

ይህ የተገለጸው "አረንጓዴ የሥራ ዕድሎችና ወጣቶች" በሚል ርዕስ በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የተጠና ጥናት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ በሆነበት መድረክ ላይ ነው።


 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት እና የጥናቱ መሪ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና እንደገለጹት የአረንጓዴ ልማት ስራ ዕድል ፈጠራ የአካባቢን ዘላቂነት ከማረጋገጥ ባሻገር ለወጣቶች ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል ወሳኝ ሚና አለው።

ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የአካባቢ ጥበቃን በማጠናከር ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር በአፍሪካ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ተግባር እያከናወነች መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይ በአረንጓዴ ልማት የሚፈጠረውን የሥራ ዕድል በሁሉም ሴክተሮች በማስፋት የወጣቱን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲሁም የአረንጓዴ ልማትን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በመሆኑም በተለይ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የአረንጓዴ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ስልጠናዎች ተገቢ ትኩረት እንዲያገኙ እንዲሁም በፖሊሲዎች ውስጥ ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸው በማድረግ ሊበረታቱ እንደሚገባም አመልክተዋል።


 

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አለበል ደሴ በበኩላቸው፣ ጥናቱ የኢትዮጵያን አረንጓዴ ዕድገት ስትራቴጂዎችና የወጣቶች የሥራ ስምሪት ዕቅዶችን እንደሚደግፍ ጠቅሰዋል።

ግኝቶቹ ወደ ተግባራዊ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች እንዲተረጎሙ ከሚመለከታቸው የመንግስት መሥሪያ ቤቶች እና የልማት አጋሮች ጋር በቀጣይ እንደሚሰራበት ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ የአካባቢ ጥበቃን የሚያጠናክር አረንጓዴ ሥራዎች ሙያዊ ሥልጠና ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የፌደራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ገነነ አበበ(ዶ/ር) ናቸው።


 

በቀጣይ የአረንጓዴ ሥራን ይበልጥ ለማስፋፋት በተለይ በቀጣሪ መሥሪያ ቤቶችና ሌሎች ተቋማት ላይ የግንዛቤ ሥራ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም