ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ሙያዊ ኃላፊነታችንን በአግባቡ እንወጣለን - መምህራን

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የተሰጣቸውን ሀገራዊና ሙያዊ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እየሰሩ መሆናቸውን የ23ኛው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊ መምህራን ገለጹ።

በ23ኛው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊ መምህራን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የትምህርት ጥራትን ማሻሻል የሁሉንም ዜጋ ትብብር የሚጠይቅ ኃላፊነት ነው።

የኢትዮጵያን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል በሚደረጉ ሀገራዊ ተግባራት ዕውቀትና ክህሎታቸውን በማሳደግ የሚጠበቅባቸውን ትልቅ ድርሻ ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ መምህር ሐብታሙ ይርጋ፤ ትውልድን የማነጽ ስራ ትልቅ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ነው ብለዋል።

ለዚህም በተከበረው የመምህርነት ሙያ ውስጥ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በእውቀት የዳበረ ትውልድን ለማፍራት ሚናቸውን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግስት የመምህራንን ህይወት ለማሻሻል የሚያከናውናቸው ተግባራት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ጉልህ ድርሻ ስላላቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከኦሮሚያ ክልል የመጡት መምህር ተክሌ መኮንን፤ የትምህርት ጥራትን የማሻሻል ተግባር የመማር ማስተማር ማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ትብብር የሚጠይቅ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል።

መምህራንም በዕውቀትና ክህሎት ላይ የተመሰረተ የመማር ማስተማር ሥርዓትን በመከተል ለትምህርት ጥራት የተሰጠንን ኃላፊነት በብቃት መወጣት ይኖርብናል ብለዋል።

ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመጡት መምህርት ገነት ሁልፋታ፤ በመንግስት የተወሰዱ የትምህርት ጥራትን ማሻሻያ የለውጥ እርምጃዎች ስኬት እያስገኙ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በዚህም የመምህርነት ሙያ የሚጠይቀውን ዕውቀትና ክህሎት በመላበስ የትምህርት ጥራት ማሻሻያ መርሃ ግብሮች ለውጥ እንዲያመጡ በማድረግ ብቁ ዜጋ ለማፍራት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም