ቀጥታ፡

የገቢ አሰባሰብ ስርዓትን በማዘመን የዜጎችን የልማት ተጠቃሚነት የሚያሻሽል የገቢ አቅም እየተፈጠረ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፦ የገቢ አሰባሰብ ስርዓትን በማዘመን የዜጎችን የልማት ተጠቃሚነት የሚያሻሽል የገቢ አቅም እየተፈጠረ እንደሚገኝ የክልሎች ገቢ ቢሮዎች ኃላፊዎች ገለጹ።

የኦሮሚያ፣ የአማራና የጋምቤላ ክልሎች የገቢ ቢሮዎች ኃላፊዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዕቅድ የተቀመጠውን ገቢ ለማሳካት በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ተስፋዬ ቱሉ፤ ዘመናዊ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት በመዘርጋት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከሚያመነጨው ሃብት የሚሰበሰበው ገቢ ዕድገት እያስመዘገበ ነው ብለዋል።

ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ እያደገ የመጣው ግንዛቤ፣ የአሰራር መሻሻያዎችና የክልሉ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴም የታክስ መሰረትን በማስፋት ለገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ ትልቅ ዕድል እየፈጠሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ክብረት ማህሙድ፤ የግብር ክፍያ አገልግሎትን የሚያሳልጡ የዲጂታል ክፍያ አማራጮች የተገልጋዮችን እንግልትና ያልተገባ ወጪ በመቀነስ ጉልህ ጠቀሜታ እያበረከቱ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ግብር ከፋዮችም የሚጠበቅባቸውን ታክስ በታማኝነትና በቅንነት በመክፈል ለሀገር ልማትና ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የጋምቤላ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ቸንኮ ዴቪድ፤ የገቢ አቅምን በማሳደግ የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በ2018 በጀት ዓመትም የገቢ ግብርን ማሻሻል የሚያስችል ግንዛቤ የመፍጠርና የዲጂታል አገልግሎት ሥርዓት የመዘርጋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ መነቃቃትን በማሻሻል ዕድገትን የሚያሳልጥ የታክስ አስተዳደር ሥርዓት በመፍጠር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም