ቀጥታ፡

የገንዘብ ፖሊሲው ጠንካራ እና ሰፋ ያለ እድገትን እየደገፈ ነው - የብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፦ የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የገንዘብ ፖሊሲው በጥብቅ ዲሲፕሊን እየተመራ ጠንካራ እና ሰፋ ያለ እድገትን እየደገፈ መሆኑን ገለጹ።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከአይ ኤም ኤፍ እና ዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባዎች ጎን ለጎን ከአለም አቀፍ ባለሀብቶች ጋር ተወያይተዋል።

በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ  ባለው አመታዊ ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙ አለም አቀፍ ባለሀብቶች ጋር በኢትዮጵያ ከፍተኛ ደረጃ የፖሊሲ ጉዳዮች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይቶችን አካሂደዋል።


 

በስታንዳርድ ባንክ ግሩፕ የተዘጋጀው የባለሃብቶች የውይይት መድረክ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ እና ከአፍሪካ የተውጣጡ ታዋቂ ባለሀብቶችን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።

በውይይቱም በአፍሪካ ኢኮኖሚ እና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ሀሳብ ለመለዋወጥ  ያስቻለ መሆኑም ተመላክቷል። 

በዚህም የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር እዮብ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ የሪፎርም ስራዎች፣ የዕድገት ሁኔታ እና እምቅ የኢንቨስትመንት እድሎች የዳሰሰ ሰፊ ማብራሪያዎችን አቅርበዋል። 

 አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማስቀጠል፣ የፋይናንሺያል ሴክተሩን ለማዘመን እና የባለሃብቶችን እምነት ለማሳደግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እያካሄዳቸው ያሉትን ሰፋፊ ጥረቶች በመዘርዘር አጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳዎች ለባለሀብቶቹ ማብራሪያ ስለመስጠታቸውም ተገልጿል።  

ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው የሪፎርም ስራዎች የዋጋ እና የፋይናንስ አካታችነትን ለማስፋፋት እና በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ስርዓትን ለማራመድ ያለመ መሆኑንም አብራርተዋል።


 

ዶክተር እዮብ አያይዘውም የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚመራና የተስተካከለ የሂሳብ አያያዝን በመጠቀም እና ቀስ በቀስ የዋጋ ንረትን ወደ ነጠላ አሃዝ ማውረድ ላይ ያተኮረ፣ ጠንካራ እና ሰፋ ያለ እድገትን እየደገፈ መሆኑን አረጋግጠዋል።  

ውይይቱ ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው ሰፋፊ የሪፎርም አጀንዳዎች ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት አላማ ያደረጉ፣ ቁርጠኝነትን የሚያረጋግጡ እና በፖሊሲ አውጪዎች እንዲሁም በአለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ማህበረሰብ መካከል ጥልቅ ውይይት ለማድረግ ወሳኝ መድረክ ሆኖ ማገልገሉም ተጠቅሷል።  

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በዘንድሮው የአይኤም ኤፍ እና የአለም ባንክ አመታዊ ስብሰባዎች ላይ የኢትዮጵያን አለም አቀፍ አጋርነቶችን ለማጠናከር፣ የፖሊሲ ግልፅነትን ለመፍጠር እንዲሁም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ተወዳዳሪና ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት በሚገባ የተቻለበት መድረክ እንደሆነም  እንዲሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም