የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተከናወኑት ተግባራት በተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻሎች እየታዩ ነው- ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተከናወኑት ተግባራት በተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻሎች እየታዩ ነው- ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

ጋምቤላ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፡- የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተከናወኑት ተግባራት በተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻሎች እየታዩ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
"የትምህርት ፍትሃዊነትና ጥራት ለትውልድ ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ 14ኛው ክልል አቀፍ የትምህርት ጉባዔ በጋምቤላ ከተማ እያካሄደ ነው።
በጉባዔው ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሀገር እድገትና ስልጣኔ እውን የሚሆነው በስነ-ምግባርና በክህሎት የታነፀ ትውልድ ማፍራት ሲቻል እንደሆነ ተናግረዋል።
ዘላቂ ልማትና እድገት እንዲረጋገጥ ጥራት ያለው ትምህርትን ተደራሽ በማድረግ በእራሱ የሚተማመን ዜጋ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የትምህርት ጥራትንና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑት ተግባራት በተለይ በተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻሎች እየታዩ መሆኑን ገልጸዋል።
በጋምቤላ ክልልም በተማሪዎች ውጤት ላይ ለውጥ መኖሩን ጠቅሰው፤ የታየውን ለውጥ ይበልጥ ለማጠናከር አመራሩ በላቀ ቁርጠኝነት እንዲሰራ አሰተያየት ሰጥተዋል።
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ላሉት ስራዎች መሳካት ሚኒስቴሩ ሁለንተናዊ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው፤ በክልሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በትምህርት ሽፋን የተሻለ ስኬት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ግን ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በክልሉ በትምህርት ሽፋን የተመዘገበውን ውጤት በጥራት ለመድገም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
የትምህርት ጉባዔው ከዛሬ ጀምሮ በሚኖረው የሁለት ቀናት ቆይታ በክልሉ የ2017 የትምህርት ዘመን አፈፃፀምን በመገምገም በ2018 የትምህርት ዘመን የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እንደሚያደርግ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ኡኩኝ ኦኬሎ ናቸው።
የትምህርት ጉባዔው በዘርፉ ያሉትን ክፍተቶችና ጥንካሬዎችን በመለየት ለቀጣይ ስራዎች የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑም ተጠቁሟል።