ቀጥታ፡

በክልሉ ቡናን በብዛትና በጥራት በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

ቦንጋ፣ ጥቅምት 6/2018 (ኢዜአ)፦  በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡናን በብዛትና በጥራት በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን አስታወቀ።

የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን ለተለያዩ የዘርፉ ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው አካላት የቡና አዘገጃጀትና ጥራት ማስጠበቅ ላይ ያተኮረ ስልጠና እየሰጠ ነው።


 

በመድረኩ ላይ በመገኘት ንግግር የደረጉት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አስራት መኩሪያ፤ በክልሉ ከቡና ልማትና ምርታማነት በተጨማሪ ለጥራት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

የቡና ምርትና ጥራት የሚረጋገጠው በሁሉም ጥረትና ትብብር ቢሆንም በተለይም የባለሙያዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም መሰረት የቡና ምርት ዝግጅትና ግብይት ሂደት የተሳለጠ እና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን የባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻዎችን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ ቡናን በብዛትና በጥራት በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በመሆኑም የቡና አምራቾችና የመፈልፈያ ኢንዱስትሪ ባለቤቶችና አርሶ አደሮች ለቡና ምርት ጥራት  ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም