ቀጥታ፡

በምሥራቅ ወለጋ ዞን  በበጋ መስኖ የስንዴ ልማት ተጠናክሮ ቀጥሏል

ነቀምቴ ፤ ጥቅምት 6/2018 (ኢዜአ) ፡- በምሥራቅ ወለጋ ዞን  በበጋ መስኖ የሚካሄድ የስንዴ ልማት ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ። 

በዞኑ   ጉቶ ጊዳ ወረዳ ጋሪ ቀበሌ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የማስጀመሪያ መርሀ ግብር ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የምሥራቅ ወለጋ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ሀላፊ ዶክተር ደረጄ ብርሃኑ እንደተናገሩት፤  በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ የግብርናው ዘርፍ ጉልህ ድርሻ አለው።


 

በዞኑ ባለፉት ዓመታት በበጋ መስኖ የስንዴ ልማት ላይ የተገኘውን ውጤት መሰረት በማድረግ በቀጣይ በተሻለ መልኩ  አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘንድሮ  የበጋ  ወቅትም የስንዴ ልማቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል  አርሶ አደሮችን በመደገፍ  እየተካሄደ መሆኑን ተናግረው፤  ለአርሶ አደሮቹ የግብዓት አቅርቦት ማመቻትን ጨምሮ  ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የጉቶ ጊዳ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ገረመው አስፋው በበኩላቸው፤  በወረዳው   በኩታ ገጠም በመስኖ ስንዴን ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በወረዳው በጋሪ ቀበሌ መልካ ዶሪ ክላስተር ጨምሮ 15 ሄክታር መሬት ላይ ልማቱ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

ከአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል  ታሪኩ ስጦታው  በሰጡት አስተያየት፤ አምና በግማሽ ሄክታር መሬት ስንዴን በመስኖ በማልማት አስር ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን በማስታወስ ዘንድሮም ተግባሩን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም