በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለግብአት አቅርቦትና ለትምህርት ቤቶች ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለግብአት አቅርቦትና ለትምህርት ቤቶች ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል

አምቦ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ) ፡-በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለግብአት አቅርቦት እና ለትምህርት ቤቶች ግንባታ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በክልሉ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጀርሳ ላፎ ወረዳ በሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት በ33 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባው ቱሉ በቾ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ግርማ ባይሳ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለግብአት አቅርቦትና ለትምህርት ቤቶች ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል።
ለአብነትም በመንግስት በጀትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ባለፉት ሶስት ዓመታት 17 ሺ 411 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ወደ አገልግሎት ገብተዋል ብለዋል ፡፡
በልማት አጋሮች ትብብርም ተጨማሪ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን ጠቅሰዋል።
በኤጀርሳ ላፎ ወረዳ በሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት በ33 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነባው ቱሉ በቾ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ተግባሩን በማስቀጠልም በተያዘው በጀት አመት በ 9 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
በሰዎች ለሰዎች ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ይልማ ታዬ በበኩላቸው፣ ትምህርት ቤቱ የተማሪዎች መማሪያ ክፍል ፣ የአስተዳደር ሕንፃና ሌሎችም አገልግሎት መስጫዎችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል ።
የምዕራብ ሸዋ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ተሾመ ፋና እንዳሉት፤ የትምህርት ቤቱ መገንባት በአካባቢው የነበረውን የትምህርት ቤቶች እጥረት በመቅረፍ ጥራት ያለውን ትምህርት ለመስጠት ያስችላል።
ወይዘሮ አለምጸሀይ ሀይሉ በበኩላቸው፤ ትምህርት ቤቱ ከመሰራቱ በፊት ልጆቻቸው ትምህርት ለማግኘት በእግራቸው ብዙ ርቀት ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ ቱሉ በቾ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ችግሩን እንደሚቀርፈው ጠቁመዋል ፡፡