ቀጥታ፡

የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ፈጣንና ቀልጣፍ ለማድረግ የሚያስችል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው- ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ 

ባሕርዳር ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ፈጣንና ቀልጣፍ ለማድረግ የሚያስችል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ። 

''የሳይበር ደህንነት የዲጂታል ኢትዮጵያ መሰረት'' በሚል መሪ ሃሳብ 6ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ዘመኑን በሚመጥን መንገድ በቴክኖሎጂ የታገዘና ደህንነቱ የተጠበቀ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በክልሉ የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ፈጣንና ቀልጣፍ ለማድረግ የሚያስችል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ ቴክኖሎጂን በማልማትና በመተግበር የተጀመሩ ስራዎች በትብብርና በቅንጀት የሚተገበሩ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የኢንፎርሜሸን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ  በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በከፍተኛ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ ላይ መሆኗን ጠቅሰው ፤ በዚሁ ልክ የሳይበር ደህንነት ጥበቃ ስራ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አስረድተዋል።


 

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመፍታት፣ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን በማስቀረት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ጊዜው የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን አንስተው፤ ከዚሁ ጋር በተገናኘ የሳይበር ደህንነትን ማስጠበቅ የግድ መሆኑን ገልጸዋል። 

የሳይበር ደህንነት ወር የመከበሩ ዓላማም ተቋማትና አጠቃላይ ሕብረተሰቡ በሳይበር ደህንነት ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን መከላከልና መቆጣጠር ብሎም በዲጂታላይዜሽን የስማርት ከተሞች እድገት ጉዞ ላይ የተቋማትን የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነት በመቀነስ ዲጂታል ኢትዮጵያን ትልም ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

6ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር ከጥቅምት 1 እስከ 30 ቀን 2018 ዓ.ም በተለያዩ መርሀ ግብሮች መከበሩ የሚቀጥል መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም