ቀጥታ፡

የትምህርት ቤቶችን ደረጃና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

ሆሳዕና፤ጥቅምት 6/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የትምህርት ቤቶችን ደረጃና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለፀ፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ እንደገለጹት የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ በማጠናከር የትምህርት ቤቶች ደረጃና የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል አቅም እየሆነ ነው፡፡

በክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ትግበራ ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ከማህበረሰቡ በማሰባሰብ የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም በተማሪዎች ውጤት፣ በስነ ምግባርና በትምህርት ፍላጎት ላይ መሻሻል እየታየ መምጣቱን ገልጸው፣ በተያዘው በጀት ዓመትም ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ ተግባሩን ለማስቀጠል እየተሰራ ነው ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በበኩላቸው በዞኑ የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በዘርፉ ማህበረሰቡን ማዕከል ያደረገ ውጤታማ ተግባር እንዲከናወን ዕድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡


 

ባለፈው በጀት ዓመት በዞኑ በንቅናቄው 556 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ሀብት በማሰባሰብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሥራ መከናወኑንም አመልክተዋል፡፡

በዚህም በትምህርት ቤቶች ምቹ የመማሪያ አካባቢን በመፍጠር የተማሪዎችን የትምህርት ፍላጎት፣ ውጤትና ስነ ምግባር በማሻሻል ረገድ ተጨባጭ ውጤት መታየት ጀምሯል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ማህበረሰቡን በማሳተፍ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ወደተግባር መገባቱን ጠቅሰው፣ በትምህርት ዘርፍ እየታየ ያለውን መሻሻል አጠናክሮ ለማስቀጠል ይሰራል ብለዋል።

የስልጤ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሹክራላ አወል በበኩላቸው በዞኑ የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በ2017 በጀት ዓመት ከ378 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ ትምህርት ቤቶችን በግብዓት ከማሟላት በተጨማሪ አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ከ460 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻልና አንድ መፅሐፍ ለአንድ ተማሪ ጥምርታን ለማሳካት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱንም ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ "የትምህርት ጥራት ለሁለንተናዊ ብልፅግና " በሚል መሪ ሀሳብ የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አጻጸምና የ2018 የትኩረት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የትምህርት ጉባኤ በወራቤ ከተማ ማካሄዱ የሚታወስ ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም