የሐረር የኮሪደር ልማት ከተማዋን ተጨማሪ ውበት እና ድምቀት አጎናጽፏታል - ኢዜአ አማርኛ
የሐረር የኮሪደር ልማት ከተማዋን ተጨማሪ ውበት እና ድምቀት አጎናጽፏታል

ሐረር ፤ጥቅምት 6/2018 (ኢዜአ)፡-የሐረር የኮሪደር ልማት ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ከመፍጠር ባለፈ ከተማዋን ተጨማሪ ውበት እና ድምቀት ያጎናፀፋት መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ።
የከተሞች የኮሪደር ልማት በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞች በመከናወኑ ለኑሮ እና ለመዝናኛ ጭምር ምቹ እንዲሆኑ አስችሏል።
በእንግዳ ተቀባይነቷና በውበቷ የምትታወቀው ጥንታዊቷ ሀረር ከተማም በዚሁ ልማት ተጨማሪ ውበትና ተመራጭ የመዝናኛ ስፍራ የተፈጠረላት መሆኑን የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱ ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ከመፍጠርም ባለፈ ከተማዋን ተጨማሪ ውበት እና ድምቀት ያጎናጸፋት መሆኑን አንስተው በዚህም ተደስተናል ሲሉ ተናግረዋል።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ጫልቱ ኡስማኢል እና አብዱልቃድር አብራሃም፤ የኮሪደር ልማቱ በተለይም የመንገድ መሰረተ ልማት የተሳለጠና ምቹ እንዲሆን አስችሏል ብለዋል።
በከተማዋ ከዚህ ቀደም የሰውና ተሽከርካሪ መንገድ ብዙም ያልተለየ ስለነበር ለአደጋ ይጋለጡ እንደነበር አስታውሰው የኮሪደር ልማቱ ለሁሉም የሚመች መሰረተ ልማት መፍጠሩን ገልጸዋል።
በሀረር ከተማ የእግረኛ መንገድን ጨምሮ የብስክሌት፣ የተሽከርካሪና የአረንጓዴ ስፍራ የተለየ በመሆኑ ለኑሮና ለመዝናኛ ምቹ ከተማ እንድትሆን አስችሏታል ብለዋል።
አቶ ወንድምአገኝ ላሽተው እና አቶ አለማየሁ ዘለቀ በበኩላቸው፤ በከተማዋ በተለያዩ አቅጣጫዎች የተገነቡት የኮሪደር ልማት ስራዎች የእግረኛ መንገድ የአረንጓዴ ልማት፣ የመዝናኛ ስፍራዎች እና የብስክሌት መንገዶችን ያሰናሰሉ በመሆናቸው ሐረርን ይበልጥ ውብና ማራኪ አድርጓታል ሲሉ ተናግረዋል።