በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ብሔራዊ ጥቅምን፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ የወል ትርክት እና የሀገር ብልፅግናን ማዕከል ማድረግ አለበት - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ብሔራዊ ጥቅምን፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ የወል ትርክት እና የሀገር ብልፅግናን ማዕከል ማድረግ አለበት

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 6/2018 (ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያን ብሔራዊ ጥቅምን፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን፣ የወል ትርክትና የሀገር ብልፅግናን ማዕከል ባደረገ መልኩ መተግበር እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገለጹ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የሚዲያ ልህቀት ማዕከል ማስጀመሪያ መርኃ ግብር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል የመገናኛ ብዙሃንና የማስታወቂያ ዘርፉ ወቅቱ በሚጠይቀው ሙያና ቴክኖሎጂ ታግዞ እንዲሰራ የባለሙያዎችና የሚዲያ ተቋማትን አቅም የመገንባት ዓላማ ያነገበ ነው።
የልህቀት ማዕከሉ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የጋዜጠኝነት ስነ ምግባር፣ ህጎችና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ስልጠና ይሰጣል ተብሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በሀገራችን ያለው ጋዜጠኝነት ኢትዮጵያን መምሰል አለበት።
በኢትዮጵያ ያሉ የግልም ይሁኑ የህዝብ ወይም የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን በአራት ጉዳዮች ላይ ልዩነት ሊኖራቸው አይገባም ብለዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ በማንኛውም መገናኛ ብዙሃን የሚሰራ ጋዜጠኛ ሊረሳው የማይገባ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያጠናክሩ፣ የህዝብን ትብብርና አንድነት የሚያሳዩ መሆን አለባቸው ብለዋል።
የወል ትርክትን መገንባት እና ኢትዮጵያ መበልጸግ አለባት የሚለውን የብልጽግና ዕሳቤ ታሳቢ አድርገው መስራት እንዳለባቸውም አፅንኦት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የመገናኛ ብዙሃን ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ብሔራዊ ጥቅም የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
የልህቀት ማዕከሉ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኝነትን የተካነ ጋዜጠኛ ለማፍራት ያግዛል ብለዋል።
የልህቀት ማዕከሉ በብቁ የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂ የተደራጀ መሆኑን ገልጸው፤ ከፖሊሲ አውጭዎች እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች፣ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።