መገናኛ ብዙሃን የሀገርና የህዝብን ጥቅም የማስከበር ተልዕኳቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው-አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን የሀገርና የህዝብን ጥቅም የማስከበር ተልዕኳቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው-አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 6/2018 (ኢዜአ)፡-መገናኛ ብዙሃን የሀገርና የህዝብን ጥቅም የማስከበር ተልዕኳቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
መንግሥት የመገናኛ ብዙሃንን ምህዳር ለማስፋት የህግና አሰራር ማሻሻያዎችን ማድረጉንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የሚዲያ ልህቀት ማዕከል ማስጀመሪያ መርኃ ግብር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ተከናውኗል።
የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል የመገናኛ ብዙሃንና የማስታወቂያ ዘርፉ ወቅቱ በሚጠይቀው ሙያና ቴክኖሎጂ ታግዞ እንዲሰራ የባለሙያዎችና የሚዲያ ተቋማትን አቅም የመገንባት ዓላማ ያነገበ ነው።
የልህቀት ማዕከሉ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የጋዜጠኝነት ስነ ምግባር፣ ህጎችና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ስልጠና ይሰጣል ተብሏል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መገናኛ ብዙሃን ትኩስና ወቅታዊ መረጃዎችን በማቅረብ ለሰላም ግንባታና ለህብረተሰብ አመለካከት ለውጥ የማይተካ ሚና አላቸው።
መንግሥት ህጎችና አሠራሮችን በማሻሻል የመገናኛ ብዙሃንን በአይነትና በቁጥር ማስፋት መቻሉን ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልፅግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የዲጂታል ጋዜጠኝነት መስፋፋት በረከት ይዞ መምጣቱን በመጥቀስ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርን የጣሱ አካላት ግን ተገቢ ያልሆነ ይዘት በማሰራጨት ላይ መሆናቸውን አንስተዋል።
ይህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ሃሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን በማሰራጨት በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ብለዋል።
በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ስነምግባርን በጠበቀ መልኩ የሀገርና የህዝብ ጥቅምን የማስከበር ተልዕኳቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የሚዲያ ልህቀት ማዕከሉ የጋዜጠኝነት ሙያ ስነ ምግባርን በማሻሻል ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ የሚዲያ ስርዓት ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል።
በሚዲያ ልህቀት ማዕከሉ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ በሚኒስትር ማዕረግ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሃላፊ እናትዓለም መለሰ፣ የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)፣ የሚዲያ ተቋማት ሃላፊዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።