ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ ሕዝቡን በማስተባበር ድጋፋችንን እናጠናክራለን - የምክር ቤት አባላት 

ደሴ፤ ጥቅምት 6/2018(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ለስኬት እንዲበቁ  ሕዝቡን በማስተባበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ  የደሴ ከተማ  አስተዳደር ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በውጭ ታሪካዊ ጠላቶችና በውስጥ ባንዳዎች እንዳይደናቀፉ ትውልዱ ታሪካዊ አደራውን ሊወጣ እንደሚገባም ተመልክቷል። 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የደሴ ከተማ ምክር ቤቱ አባላት፤  የተጠናቀቁ እና በሂደት ላይ ያሉ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስኑ መሆናቸውን አንስተዋል።

በመሆኑም ለፕሮጀክቶቹ ስኬት የመንግስት ጽናትና ቁርጠኝነት እንዳለ ሆኖ የሕዝቡ ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ ሰይድ እንድሪስ እና አቶ ሰይድ በላይ፤ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በውጭ ጠላቶችና በውስጥ ባንዳዎች እንዳይደናቀፉ ትውልዱ ታሪካዊ አደራውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ከጥንት እስካሁን ሀገሪቱ ሃብቷን አልምታ እንዳትጠቀም ብዙ መጣራቸውን አስታውሰው፤  በመንግስት ብርቱ ጥረትና በሕዝቡ ፅናት ታላቁ የኢትዮጵያ  ህዳሴ ግድብ እውን መሆኑን አንስተዋል።


 

የህዳሴ ግድብ ከኃይል ልማት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለውና ኢትዮጵያ ሃብቷን መጠቀም መጀመሯ ሁላችንንም ያስደሰተ ነው ሲሉም ተናግረዋል። 

ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ ፈንታዬ አብርሃ፤ የአሁኑ ትውልድ በጀግንነት ሀገሩን በመጠበቅና ሃብቱን አልምቶ በመጠቀም ታሪክ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በቀጣይም በሀገሪቱ የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና የሚያረጋግጡ በመሆናቸው ለስኬታቸው በጋራ መትጋት አለብን ብለዋል።

በመሆኑም የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በውጭ ታሪካዊ ጠላቶችና በውስጥ ባንዳዎች እንዳይደናቀፉ ትውልዱ ታሪካዊ አደራውን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹ  በፍጥነት ለስኬት እንዲበቁ  ሕዝቡን  በማስተባበር ድጋፋቸውን ይበልጥ አጠናክረው  የድርሻቸውን እንደሚወጡ የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም