የዩኒቨርሲቲ -ኢንዱስትሪ ትስስር ፈጠራና ቴክኖሎጂዎችን ለማስተላለፍ ሚናው የጎላ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዩኒቨርሲቲ -ኢንዱስትሪ ትስስር ፈጠራና ቴክኖሎጂዎችን ለማስተላለፍ ሚናው የጎላ ነው

ሐረማያ ፤ጥቅምት 6/2018 (ኢዜአ)፡- የዩኒቨርሲቲ -ኢንዱስትሪ ትስስር ፈጠራና ቴክኖሎጂዎችን ከማስተላለፍ አንፃር ሚናው የጎላ መሆኑ ተገለጸ።
የምስራቅ ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ፎረም ምስረታ የምክክር መድረክ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት አብዲ መሀመድ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ትስስሩ ለኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆኑ አዳዲስ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን ይበልጥ ለማውጣት ያግዛል።
የሁለቱ ተቋማት ትስስር መጠናከር የሰለጠነ የሰው ሃይልን ከማፍራት በተጨማሪ ለስራ ፈጠራና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከማፍለቅ አኳያ ሚናው የላቀ ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር ከተቀናጁ በተግባርና ንድፈ-ሃሳብ የዳበረ የሰው ሃይል በማፍራት አገራዊ የልማት እቅዶችን ለማሳካት ጉልህ ሚና አላቸው ሲሉም አክለዋል።
ዩኒቨርሲቲውም በአቅራቢያው ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጋር የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው መድረኩ የጋራ ግንዛቤ ለመያዝና ቀጣይ ስራዎች ላይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የተቋማት ትስስር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዴስክ ሃላፊ አቶ ተሾመ ዳንኤል በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር ማስተሳሰር በተግባርና ንድፈ-ሃሳብ የዳበረ የሰው ሃይል ለማፍራት ያስችላል።
እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ የሚከናወኑ ችግር ፈቺ ምርምር ስራዎችን ወደ ማህበረሰቡ እንዲዳረሱና ወደ ውጤት እንዲቀየሩ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ፈጠራና ቴክኖሎጂዎችን ከማስተላለፍ አንፃርም ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አመልክተዋል።
የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስሩ በአዋጅ የተደገፈ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ቀድሞ የነበሩ ክፍተቶችን ለማረም እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
በፎረም ምስረታው የምክክር መድረክ ላይ የሐረማያ፣ ድሬዳዋ፣ ሰመራ፣ ጅግጅጋ፣ ኦዳ ቡልቱና ቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲዎች፣ የትምህርት ሞያ ስልጠና ኮሌጆች እንዱሁም በቀጠናው የሚገኙ የመንግስት እና የግል ኢንዳስትሪ ተወካዮች ተገኝተዋል።