ቀጥታ፡

የደመወዝ ማሻሻያው የዜጎችን ችግር ለመፍታትና የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የመንግስት ቁርጠኝነት የታየበት ነው

ጂንካ፤ጥቅምት 6/2018 (ኢዜአ)፡-የደመወዝ ማሻሻያው የዜጎችን ችግር ለመፍታትና የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የመንግስት ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጂንካ ከተማ የመንግስት ሠራተኞች ተናገሩ።

የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻልና የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል በበጀት ዓመቱ ከመስከረም ወር ጀምሮ ለመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ ለማድረግ መወሰኑ ይታወሳል።

የደመወዝ ማሻሻያው በተለይም ዝቅተኛ ተከፋይ የሆኑ የመንግስት ሠራተኞችን የኑሮ ጫናን በማቃለል ረገድ ትርጉም ያለው መሆኑ ይታወቃል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ በጂንካ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ማሻሻያው የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የመንግስት ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑን በማንሳት በጭማሪው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የደመወዝ ማሻሻያው በአሁኑ ወቅት ያለውን የኑሮ ጫና ያገናዘበ በመሆኑ ኑሮን ለመቋቋም የሚያግዝ መሆኑን አንስተው ስራቸውን በተሻለ ትጋት ለማከናወን መነሳሳት የፈጠረላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

በአሪ ዞን ገቢዎች መምሪያ የምጣኔ ሀብት ጥናት ባለሙያ ሀብታሙ ዲዳ፤ መንግስት የወቅቱን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ለመንግስት ሠራተኛው የደመወዝ ማሻሻያ ማድረጉ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የደመወዝ ማሻሻያው የኑሮ ጫናን ከማቃለልም ባለፈ ለስራ ጥሩ ተነሳሽነትን ያመጣ ስለመሆኑም አንስተዋል።

በክልሉ ትምህርት ቢሮ ውስጥ የሚሰሩት አቶ ሳሙኤል ሻሌቦ እና በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የጂንካ ቅርንጫፍ የሚሰሩት ወንድማገኝ በቀለ፣ የደመወዝ ማሻሻያው እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋምና ለሰራተኛው የስራ ብርታት ተጨማሪ አቅም መሆኑን ነው የገለጹት።


 

የአሪ ዞን ፐብሊክ ሰርቪስ መምሪያ ኃላፊ አሸብር ገልሶ፤ የደመወዝ ጭማሪው የኑሮ ሁኔታን ታሳቢ ያደረገና ሰራተኞችን ይበልጥ ለማበረታታት ያለመ መሆኑን አንስተዋል።


 

በመሆኑም ሠራተኞች ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል እንዲሁም ውጤታማ ሥራዎችን በማከናወን ለተደረገው ጭማሪ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም