ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የመስኖ ልማትና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ነው

አዲስ አበባ፤ጥቅምት 6/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የመስኖ ልማትና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለጹ።

የአማራ ክልል የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የመስኖና የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች ንቅናቄ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በደብረ ብርሃን ከተማ ልቼ ቀበሌ ተካሂዷል።


 

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)፣ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እና ሌሎች የክልሉ ስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የመስኖ ልማትና የተቀናጀ የአካባቢ ጥበቃ ስራን በልዩ ትኩረት መምራት የሚያስችል ንቅናቄ በየዓመቱ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

የመስኖ ልማትና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ የግብርና ምርታማነትን ለማረጋገጥ ቁልፍ ተግባር ተደርጎ እየተሰራበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የግብርና ምርታማነትን ለማሻሻል የሚተገበሩ የንቅናቄ መርሃ ግብሮችም የአፈር ለምነትን በማሻሻል፣ የአካባቢ ጥበቃን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በአማራ ክልል ያለውን በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት ታሳቢ በማድረግ በተቀናጀ ዕቅድ የግብርና ምርታማነትን ማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎች በትኩረት እየተሰራባቸው እንደሚገኙ አንስተዋል።

በቀጣይም የግብርና ምርታማነት ውጤታማነትን የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ በድሉ ውብሸት፤ ለከተሞች መዘመንና መስፋፋት የተሰጠው ትኩረት ዕድሜ ጠገብ ታሪክ ላላት ደብረ ብርሃን  ልዩ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።


 

የደብረ ብርሃን ከተማን ለማዘመን ከሚሰሩ ስራዎች በተጨማሪ በስንዴና ቢራ ገብስ ክላስተር የግብርና ሥርዓት ምርታማነትን የሚያሳድጉ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

የመስኖና የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች የማስጀመሪያ የንቅናቄ መርሃ ግብርም የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም