የዳልጋ ከብት ዝርያን በማሻሻል የወተትና የስጋ ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዳልጋ ከብት ዝርያን በማሻሻል የወተትና የስጋ ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

መቱ ፤ጥቅምት 6/2018 (ኢዜአ)፡-በኢሉባቦር ዞን የዳልጋ ከብት ዝርያን በማሻሻል የወተትና የስጋ ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ አወል መሐመድ ፤ እየጨመረ የመጣውን የእንስሳት ውጤቶች ፍላጎት ለማሟላት የእንስሳቱን ዝርያ ማሻሻል ላይ ትኩረት መሰጠቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ለዚህም በሰው ሰራሽ ዘዴ በማዳቀል የዳልጋ ከብቶችን ዝርያ በማሻሻል የስጋም ሆነ የወተት ምርት በማሳደግ የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
ዝርያቸው ከተሻሻሉ ላሞች በአማካይ ከስምንት እስከ አስር ሊትር ወተት መገኘቱን ጠቅሰው፤ ይህም ውጤት ከተለምዶው ዝርያ ከሶስት እጥፍ በላይ ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል።
በሰው ሰራሽ እንስሳት ከተዳቀሉ ላሞቻቸው የተሻለ የወተት ምርት በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በዞኑ የዲዱ ወረዳ አርሶ አደር አለሙ መሸሻ ናቸው።
በዝርያ ማሻሻል ስራው የሚወለዱ ጥጆች የዕድገት ፍጥነትና የገበያ አዋጭነቱ የላቀ በመሆኑ ልማቱ ከቀድሞ ይበልጥ ተጠቃሚ መሆን እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
አርሶ አደር አዛሉ ለሙ ፤ በሰው ሰራሽ ዘዴ በማዳቀል የተወለደን ወይፈን ተንከባክበው በማሳደግ በጥሩ ዋጋ መሸጣቸውን ተናግረዋል።
የእንስሳት ዝርያዎች ማሻሻያው ከልማዳዊው አረባብ ትልቅ ልዩነት በመኖሩ በአጭር ጊዜ የወተትም ሆነ የስጋ ምርት መስጠት እንደሚያስችል አንስተዋል።
አቶ ዕድገት አሰፋ በበኩላቸው፤በሰው ሰራሽ መንገድ ከተሻሻሉ ላሞቻቸው በቀን እስከ ስምንት ሊትር ወተት እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከግብርና ጽሕፈቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በኢሉባቦር ዞን ባለፉት ሁለት ዓመታት በሰው ሰራሽ የዝርያ ማሻሻል ከ34 ሺ በላይ እንስሳትን ማዳቀል ተችሏል።